የህወሓት አማጺያን ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች እንዲወጡ አሜሪካ ጠየቀች

የህወሓት አማጺያን ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች እንዲወጡ አሜሪካ ትጠይቃለች ሲሉ የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር አስታወቁ።

ሳማንታ ወታዳራዊ አማራጭ ለግጭቱ መፍትሄ መሆን ስለማይችል በትግራይ ክልል የሚገኙ የአማራ ክልል ኃይሎችም ይውጡ ሲሉ ጠይቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ያለው የኤርትራ ሠራዊት በአስቸኳይ እና ለጨመረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ መውጣት አለባቸው ሲሉ ሳማንታ የአገራቸውን አቋም በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ሳማንታ ጨምረውም "በትግራይ ለሚገኙ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ሁሉም አካላት ግጭት ማቆም አለባቸው። ለዚህ ግጭት ወታደራዊ መፍትሄ አማራጭ አይደለም" ሲሉ አስፍረዋል።

ምዕራባውያን አገራት የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ለቀው ይውጡ ሲሉ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት በሱዳን የሚገኙት ሳማንታ፤ የሱዳን ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ኢትዮጵየ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዩኤስኤይድ ኃላፊዋን የኢትዮጵያ ጉዞ በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ላይ ሳማንታ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙት "በትግራይ ክልል ረሃብ እንዳይከሰት የተሟላ እና ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ግፊት ለማድረግ ነው" ብሎ ነበር።

ሳማንታ በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይገናኛሉ የተባለ ሲሆን፤ የዩኤስኤይድ እና የዩኤስኤይድ አጋር ድርጅቶች በኢትዮጵያ የሚያከናውኑትን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሥራዎችንም ይጎበኛሉ ተብሏል።

ሳማንታ እስካሁን በሱዳን ባላቸው ቆይታ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ሸሽተው በሱዳን ተጠልለው የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ተፈናቃዮችን መጎብኘታቸውን የተራድኦ ድርጅቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ወደ 46 ሺህ ለሚጠጉ ስደተኞች ዩኤስኤይድ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን ሳማንታ ከተፈናቃዮች ጋር ተነጋግረዋል።

"አስተዳዳሪዋ በኡማ ራኩባ ተጠልለው ከሚገኙ ሴቶች ጋር ተነጋግረዋል። በታጠቁ ሰዎች የተፈጸሙ እጅግ አስከፊ የሆኑ የጾታዊ ጥቃት ታሪኮችን ሰምተዋል" ይላል የእርዳታ ድርጅቱ መግለጫ።

ሳማንታ በሱዳን ቆይታቸው ለሰብዓዊ እርዳታ ግልጋሎት የሚውል ተጨማሪ 56 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉን ይፋ አድርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አስተዳዳሪዋ ጉብኝታቸው ወቅት አሜሪካ አባል ያልሆነችበት ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን ሱዳን ለመቀላቀል መወሰኗን ይፋ አድርገዋል።

ሳማንታ ፓዎር ማን ናቸው?

ሳማንታ ፓዎር ወደ አሜሪካ መንግሥት መንበረ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ጋዜጠኛ ነበሩ። በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የተደረጉ ጦርነቶችን በስፋት ዘግበዋል።

በፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ዘመን የፕሬዝደንቱ ከፍተኛ አማካሪ እና በተባባሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደርም በመሆን አገልግለዋል።

ሳማንታ በኦባማ አስተዳደር ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበራቸው ከሚያስብሉ ምክንያቶች አንዱ፤ የሊቢያውን የቀድሞ መሪ ሙአመር ጋዳፊን ከሥልጣን ለማውረድ አሜሪካ የጦር አማራጭን እንድትጠቀም የኦባማ አስተዳደር ላይ ጫና ማሳደራቸው አንዱ ነው።

በፎርብስ የ2016 የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ 100 ሴቶች ዝርዝር ውስጥ መካተት ችለዋል።

የ50 ዓመቷ ሴት በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ መንግሥት እርዳታ ድርጅት የሆነውን ዩኤስኤይድን በበላይነት ይመራሉ።