ፖሊስ ተወከልን ጨምሮ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተሳትፈዋል ያላቸውን 6 ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን ዘጋ

የፌደራል ፖሊስ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተሳትፈዋል ያላቸውን 6 ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን መዝጋቱን አስታወቀ።

ፌደራል ፖሊስ ከወንጀሉ ጋር ቀጥተኛ ተሳትፎ አላቸው በሚል የዘጋቸው ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ተወከል ኤክስፕረስ፣ አመል፣ ጁባ፣ 24 ኦላይን እና ታጅ የተሰኙ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች እንደሚገኙበት የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጄይላን ጨምረው ከላይ የተጠቀሱት ድርጅቶች ተወካዮች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በተጨማሪ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብሏል። ፌደራል ፖሊስ በፌስቡክ ገጹ ላይ በ14 ባንኮች የተከፈቱና ከ10 ሚሊየን ብር በላይ የያዙ ከመቶ በላይ የባንክ የሂሳብ ደብተሮች ከግለሰቦቹ ጋር በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ብሏል።

ተጠርጣሪዎቹ የአሜሪካ ዶላር ከአዲስ አበባ በጥቁር ገበያ እየሰበሰበ መንግሥትን እንዲዳከም ሲሰሩ የተደረሰባቸው ናቸው ተብሏል።

ህወሓት ቀድሞ ከአዲስ አበባ እስከ ቶጎ ውጫሌ በዘረጋው ኔትዎርክ አማካኝነት በንግድ ተቋማት የሚሰበሰቡትን የውንጪ ምንዛሬ በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጣ በማድረግ "ለሽብር ቡድኑ ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ" ነው ብሏል የፌደራል ፖሊስ።

"ጁንታው በአዲስ አበባ ህጋዊ አሰራርን ሽፋን በማድረግ መንግስት እንዲዳከምና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገባቸው ጥሬ እቃዎች የዶላር እጥረት እንዲያጋጥመው እንዲሁም የኑሮ ውድነትን አባብሶ ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ የሞከረ መሆኑንም ድርሼበታለሁ ብሏል"