ፖፕ ፍራንሲስ ከተደረገላቸው ቀዶ ህክምና በኋላ 'መሻሻል' እያሳዩ ነው ተባለ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ሮም በሚገኝ ሆስፒታል ያጋጠማቸውን የአንጀት ችግርን ለማከም የተሳካ ቀዶ ጥገና እንደተደረገላቸው ቫቲካን አስታወቀች።

የ84 ዓመቱ ፖፕ ፍራንሲስ በአጠቃላይ ማደንዘዣ ድጋፍ ለተደረገው ህክምና "ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል" ሲሉ የቫቲካን ቃል አቀባይ ማቲዎ ብሩኒ ተናግረዋል።

ፖፕ ፍራንሲስ እአአ 2013 ላይ ከተመረጡ በኋላ ሆስፒታል ሲገቡ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

አርጀንቲናዊው እሁድ ዕለት በሺህዎች ለሚቆጠሩ ጎብኝዎች በቅዱስ ፒተር አደባባይ ተገኝተው መልዕክት አስተላለፈዋል።

ቫቲካን ቀደም ሲል በሰጠችው መግለጫ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ባጋጠማቸው የአንጀት ህመም ምክንያት በጌሜሊ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቃለች።

የገጠማቸው ሲምፕቶማቲክ ዳይቨርቲኩላር ስቴኖሲስ የተሰኘው ህመም በትልቁ አንጀት ግድግዳ ላይ እብጠትን የሚያስከትል ሲሆን ይህ የአንጀት ወደ መጥበብ ሊያመራ ይችላል ተብሏል።

ከምልክቶቹ መካከል የሆድ መነፋት እና ተደጋጋሚ የሆድ ህመም ተጠቃሾች ናቸው።

ቫቲካን ስለ ቀዶ ህክምናው እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሆስፒታል ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አልሰጠችም።

ፖፕ ፍራንሲስ እሁድ በሴንት ፒተር አደባባይ ባደረጉት የበረከት ንግግር ወቅት በመስከረም ወር ወደ ስሎቫኪያ እንደሚሄዱ አስታውቀው ቀደም ብለው ግን በሃንጋሪ ዋና ከተማ በቡዳፔስት ቅዳሴ እንደሚመሩ ተናግረዋል።

እአአ በ1936 በቦነስ አይረስ የተወለዱት ፍራንሲስ በ21 ዓመታቸው የቀኝ ሳንባቸውን የተወሰነ ክፍል አጥተዋል።

እአአ በ 2014 በሆድ ህመም ምክንያት በርካታ ፕሮግራሞቻቸውን ሰርዘው ነበር ተብሏል።