ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባለፈው ሳምንት ግማሽ አካሉ ተቦድሶ በርካቶች የሞቱበት ሕንፃ ሙሉ በሙሉ ወደመ
በአሜሪካዋ ማያሚ ከተማ ግማሽ አካሉ ተደርምሶ ለርባከቶች ሞት ምክንያት የሆነው ሕንፃ ከደህንነት ጋር በተያያዘ ሙሉ በሙሉ እንዲወድም ተደረገ።
በፍሎሪዳ ግዛት ማያሚ ከተማ የሚገኘው የዚህ ሕንፃ ቅሪተ አካል እንዲወድም ተቀጣጣይ ፈንጂዎች ጥቅም ላይ ውለዋል።
12 ፎቆች ያሉት ቻምፕሌይን ታወርስ ሳውዝ የተሰኘው የመኖሪያ አፓርትማ ግማሽ አካል በፈረንጆቹ ሰኔ 24 ተደርምሶ በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
እስካሁን ድረስ 24 ሰዎች እንደሞቱ ሲታወቅ 121 ሰዎች የገቡበት አልታወቀም።
የተቀረውን የሕንፃውን ክፍል ማውደም ያስፈለገው የጠፉ ሰዎችን ያለምንም ስጋት ማፈላለግ እንዲያመች ነው።
የት እንደገቡ ያልታወቁ ሰዎችን ፍለጋው የተቀረው የሕንፃው ክፍል እስኪወድም ድረስ እንዲቆም የተደረገ ሲሆን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ፍለጋቸውን ወዲያውኑ ቀጥለዋል።
ነገር ግን እስካሁን ድረስ መጀመሪያ ከፈረሰው የሕንፃው አካል ምንም ዓይነት ሰው በሕይወት አልተገኘም።
የተቀረው የሕንፃው አካል ይፍረስ የሚሉ ድምፆች መሰማት የጀመሩት ትሮፒካል ስቶርም ኤልሳ የተሰኘ አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ ወደ ፍሎሪዳ ግዛት እየገሰገሰ መሆኑን ተከትሎ ነው።
እሁድ ዕለት የማያሚ ከተማ ከንቲባ ቻርልስ በርኬት ይህ አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ ለአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ፍለጋውን የከበደ ያደርግባቸዋል ሲሉ ተደምጠው ነበር።
ሕንፃውን ያፈረሱት ከዚህ በፊት አንድ ሕንፃ ምንም ሳይነካ በፈንጂ ቁጭ በማድረግ የተካኑ ሰዎች ናቸው።
ሕንፃው ከመፍረሱ በፊት የአካባቢው ባለሥልጣናት ሕንፃው አጠገብ የሚኖሩ ሰዎች ቤታቸው እንዲቀመጡ እንዲሁም በርና መስኮታቸውን ቢያንስ ለሁለት ሰዓታት እንዲዘጉ አሳስበው ነበር።
የማያሚ ዳዴ ግዛት ከንቲባ የሆኑት ዳኒዬላ ሌቪን ካቫ በበኩላቸው የቤተሰብ አባል ለጠፋባቸው ሰዎች ሐዘኔታቸውን ገልፀው የተቀረውን የሕንፃውን ክፍል ለቀው የወጡ ሰዎችን አፅናንተዋል።
ከፈረሰው ሕንፃ በቀር በአካባቢው ያሉ አፓርትማዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ግን ቤታቸው እንዲቀመጡ እንጂ ለቀው እንዲወጡ አልተነገራቸውም።
ሕንፃውን ያፈረሱት ባለሙያዎች ድሮንና ሌሎች ካሜራዎችን ተጠቅመው ነው ምንም ጥፋት ሳያደርሱ ግማሹን ሕንፃ ከጥቅም ውጭ ያደረጉት።
ከፈረሰው ሕንፃው የወጡ ሰዎች ተተኪ መኖሪያ ቤት ይሰጣቸው አይሰጣቸው እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
የአካባቢው ባለሥልጣናት ሌሎችም በአካባቢው ያሉ ሕንፃዎች ምናልባት የመደርመስ አደጋ ካለባቸው በሚል ምርመራ እያደረጉ ይገኛሉ።
40 ዓመት የሞላው ቻምፕሌይን ታወርስ ሳውዝ የተሰኘው የመኖሪያ አፓርትማ በምን ምክንያት እንደተደረመሰ እስካሁን ግልፅ አይደለም።