በበጎ ስራቸው የሚታወቁት አበበች ጎበና አረፉ

በበጎ ስራዎቻቸው የሚታወቁት አበበች ጎበና ዛሬ ጥዋት ሰኔ 27/2013 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ቢቢሲ ከቤተሰቦቻቸው ማረጋገጥ ችሏል።

አበበች ጎበና ሕፃናት ክብካቤና ልማት ማሕበር (አጎሕልማ) የተሰኘው ድርጅታቸውም ማረፋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገፁ አስታውቋል።

"ልብ የሚሰብር ነው። በአለማችን ካሉ ድንቅ ሴቶች አንዷና የአፍሪካዋ ማዘር ቴሬሳ ዶክተር አበበች ጎበና ዛሬ ጥዋት አርፈዋል" በማለት ገፁ መልዕክቱን አስፍሯል።

ዶ/ር አበበች ጎበና (እዳዬ) በቅርቡ በኮቮድ-19 ተይዘው በጳውሎስ ሆስፒታል በፅኑ ህሙማን ማዕከል ህክምና እየተደረገላቸው የቆየ መሆኑ ይታወሳል።

የክብር ዶክተር አበበች ጎበና ማን ነበሩ?

ዶ/ር አበበች ጎበና በዚያን ወቅት ሸዋ ተብሎ በሚጠራው ክፍለ ሃገር ሰላሌ አውራጃ ሸበል በምትባል የገጠር መንደር በአውፓውያኑ 1938 ተወለዱ።

አበበች ጎበና ሕፃናት ክብካቤና ልማት ማሕበር (አጎሕልማ) ካሰፈረው የሕይወት ታሪካቸው እንደተገኘው አባታቸው ከጣልያን ጋር በነበረው ጦርነት የተገደሉ ሲሆን አበበች እስከ ዘጠኝ አመታቸው ያደጉት በአያቶቻቸው ቤት ነው።

በዘጠኝ አመታቸው በነበረው ባህል መሰረት ተገደው እንዲጋቡ ተደረጉ በወቅቱም ደስተኛ አልነበሩም ይባላል።

በኋላም በአዲስ አበባ መጥተው መሰረታዊ የሚባል ትምህርት የተከታተሉ ሲሆን በአንድ ኩባንያ ውስጥ በጥራት ተቆጣጣሪነት ስራ አገኙ።

አበበች ጎበና በኢትዮጵያ ውስጥ ቀደምት የተባለውንና ሕፃናት ክብካቤና ልማት ማሕበር (አጎሕልማ) የተሰኘ ወላጅ አልባዎች ህፃናት ማሳደጊያ መስራች ናቸው።

ለዚህም መነሻ የሆነው በወሎ በሚገኘው የግሸን ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ለመሳለም ሃይማኖታዊ ጉዞ ባደረጉበት ወቅት ነው።

ቦታው በረሃብ ተጠቅቶ የነበረ ሲሆን ከጉዟቸው ሲመለሱም አንድ ህፃን ልጅ ከሞተችው እናቱ አጠገብ ተኝቶ አዩ።

ልጁንም አንስተው ወደ ቤታቸው ወሰዱት። በዚህም አላበቃም ከሞተ አባቱ አጠገብ ተኝቶ ያገኙትንም ሁለተኛ ህፃን ልጅ እንዲሁ ወደ ቤታቸው ወሰዱ።

በአንድ አመት ውስጥም 21 ወላጅ አልባ ህፃናትን ለማሳደግ ወደቤታቸው ያመጡት አበበች ጎበና ፍቅርና ደግነታቸውም ለሶስት አስርት አመታት አብሯቸው ቀጠለ።

በራሳቸው ጥረት ብቻ የነበረው ሁኔታ ተቀይሮ ቀስ በቀስም እርዳታ ማግኘት የጀመሩት አበበች በአውሮፓውያኑ 1986 የወላጅ አልባ ህፃናት ማሳደጊያቸውን አስመዘገቡ።

የአበበች ጎበና ወላጅ አልባ ትምህርት ቤት በአዳሪነት 200 ተማሪዎችን እንዲሁም 482 ተመላላሽ ተማሪዎችን እንደሚያስተምር ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

ያሳደጓቸው ልጆች 'እዳዬ' ብለው ይጠሯቸዋል። ይህ ስም ዛሬ የሚሠሩትን እንደሚገልጽ እምነታቸው ነው።።

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ተጋላጭ ለሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች ድጋፍ መደረጉን አበበች ጎበና የመሰረቱት አበበች ጎበና ሕጻናት ክብካቤ ልማት ማኅበር ይገልጻል።

ለዚህ መልካም ተግባራቸው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለአበበች ጎበና የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መስጠቱ ይታወሳል።