በትግራይ የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶች ሊመለሱ እንደሚገባ ኢሰመኮ ገለፀ

በትግራይ የመብራት፣ የስልክ፣ ውሃና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ሊመለሱ እንደሚገባና በክልሉ ስላለው የፀጥታ ሁኔታና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በቂ መረጃ መስጠት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

ኢሰመኮ በትናንትናው ዕለት ሰኔ 21፣ 2013 ዓ.ም 'የሲቪል ሰዎችን ሁኔታ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል' በሚለው መግለጫውም ነው ይህንን ያሰፈረው።

የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ በትግራይ የግንኙነት መስመሮች መቋረጣቸውን ያስታወሰው መግለጫው የነዋሪዎች ደህንንነትንም ለማስጠበቅ የሚረዱ እርምጃዎችም መወሰድ ይገባቸዋል ብሏል።

ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለመፈለግ የሚደረገው ጥረትና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጥበቃና ለተደራሽነቱ ትብብርን ያበረታታው መግለጫው የሰላማዊ ዜጎች ደህንነትና ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም አስምሯል።

በክልሉ የመብራት የስልክ፣ የውሃ መሰረታዊ አገልግሎቶች በመቋረጣቸውም በነዋሪዎች ላይ ከባድ የኑሮ ጫናን እያስከተለ እንደሚገኝም ተመልክቷል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ የባንክና የጤና አገልግሎትን አቅርቦት ላይ ችግሩን አባብሶታል ብሏል ኢሰመኮ በመግለጫው።

የነዚህ መሰረታዊ አገልግሎቶች መቋረጥ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሃገራዊና ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች የሰብዓዊ ድጋፉን በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳው መግለፃቸውን አካቷል።

ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎችምንም ሆነ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ስለሚገኙበት ሁኔታም ለማወቅ ፈታኝ አድርጎታል ማለታቸውንም ኢሰመኮ ያስረዳል።

"በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች ስላሉበት ሁኔታ የተገቢው መረጃ ማነስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚደመጡ ዘገባዎችና ንግግሮች ጋር ተዳምሮ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ የሚጥል ነው።" በማለት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለን ዋቢ

በማድረግ መግለጫው አስፍሯል።

የትግራይ ክልል ለአስቸኳይ እርዳታ ክፍት እንድትሆንና የመገናኛ፣ መብራትና የትራንስፖርት አገልግሎቶች አንዲቀጠሉም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየጠየቁ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ የመቀለና የሽረ አየር ማረፊያዎች ክፍት እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

የተቸገሩ ሰዎችንም ለመድረስ ከአየር ማረፊያዎች በተጨማሪ የመብራትና የመገናኛ ዘዴዎች እንዲቀጠሉ ጠይቀዋል።

የአውሮፖ ሕብረት የውጭ እና የደኅንነት ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው ታማኝ የሆነ የተኩስ አቁም ማለት አስቸኳይ እርዳታ የሚፈልጉ ሚሊዮኖች ህፃናት፣ ሴቶችና ወንዶች እንዲደርሳቸው የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ነው ብለዋል።

ኮሚሽነሩ እንዳሉት "የተኩስ አቁሙ በሁሉም በግጭቱ ተሳታፊ በነበሩ ወገኖች ሁሉ በቁርጠኝነት መከበር እና የመሰረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መመለስ፣ አጠቃላይ ሁኔታውን ለማሻሻል፣ በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ፣ እንዲሁም ሰብአዊ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው።" ብሏል

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ዩኒቨርስቲዎች ተመድበው የሚማሩ ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት ስላሉበት ሁኔታ ቤተሰቦች ባለመወቃቸው መንግሥትን ማብራሪያ እየጠየቁ እንደሚገኙም ጠቅሶ የነዋሪዎችን ደህንነት ማረጋገጥ የመንግሥት ግዴታ መሆኑንም አስታውሷል።

ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችና የሚዲያ ሰዎች እንዲሁም ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታም እየተከታተለ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ይህም ሁኔታ በነዋሪዎች ላይ ማንነትን መሰረት ባደረገ ለጥርጣሬ እና መድልዎ የሚያጋልጥ ተግባር እንዳይሆንም ስጋት እንዳሳደረበት ኮሚሽኑ አስታውቋል።

" ማንኛውም አይነት እስር ሁልጊዜም ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን ይገባል" በማለትም ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ሁኔታውን ከማባባስ፣ በህዝቦች መካከል ጥላቻና ጥርጣሬን ሊፈጥሩ ከሚችሉ ንግግሮች ሊቆጠቡ ይገባልም ሲል ምክሩን ለግሷል።