ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰው ሠራሽ ረሃብ በትግራይ የፈጠረው ቀውስ
- ፀሐፊ, *አሌክስ ደ ዋል
- የሥራ ድርሻ, የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ
የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርክ ሎውኮክ "ትግራይ ውስጥ ረሃብ ተከስቷል" ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ከቡድን 7 አገራት ጉባኤ በፊት በተካሄደ ውይይት ነበር ይህንን ያሉት። የንግግራቸው መነሻ የተባበሩት መንግሥታት የሚደግፈው ኢንተግሬትድ ፉድ ሰኪውሪቲ ፌዝ ክላሲፊኬሽን (አይፒሲ) በትግራይ የሠራው ዳሰሳ ነው።
ትግራይ ውስጥ ወደ 353,000 ገደማ ሰዎች ደረጃ አምስት የሚባለው (catastrophe) ማለትም የከፋ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙና፤ ተጨማሪ 1.769 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ደረጃ አራት የሚባለው (emergency) ማለትም አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያሻቸው ጠቁመዋል።
ይህ አገላለጽ "ረሃብ ተከስቷል" ማለት ነው። በእርግጥ አይፒሲ ፖለቲካዊ ስሱነትን ከግምት በማስገባት "ረሃብ" የሚለውን ቃል አልተጠቀመም። የኢትዮጵያ መንግሥትም "ረሃብ" የሚለውን አይቀበልም።
ከእነዚህ ቁጥሮች ጀርባ በርካቶች አሰቃቂ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ። በርካቶች በረሃብ ሳቢያ መሞታቸው አይቀርም።
አሁንም በረሃብ የሞቱ ሰዎች አሉ።
በትግራይ ገጠራማ አካባቢዎች ሲራቡ አድረው ጠዋት አስከሬናቸው የተገኘ ሰዎች እንዳሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በወታደሮች ታግተው የወሲብ ብዝበዛ ሲደርስባቸው የነበሩና አሁን በሕክምና መስጫ ወይም መጠለያ ያሉ ሴቶች ሰቆቃ ውስጥ ናቸው።
በግዳጅ የተነጠሏቸው ልጆቻቸው በረሃብ ሞተው ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ሰላም ነስቷቸዋል።
ምግብ ያጣ ሰውነት ላለመሞት የሚታገለው የዛን ሰው የአካል ክፍሎች እየተመገበ ስለሆነ በረሃብ መሞት እጅግ የከፋ ሞት ነው።
የመጀመሪያ ተጠቂዎች ሕፃናት ሲሆኑ፤ በረሃብ ወቅት ከሚሞቱት ሁለት ሦስተኛውን ይይዛሉ።
በቅርቡ በወጣ ሪፖርት መሠረት 300,000 ልጆች ይሞታሉ ተብሎ ተፈርቷል።
ይህን ዳሰሳ የሠራው ቡድን መላው ትግራይን ማዳረስ አልቻለም። ስለዚህም አጠቃላይ ቁጥሩ ከዚህ ሊበልጥ ይችላል።
በቤልጄም ጋንት ዩኒቨርስቲ የተሠራው 'ትግራይ ሂውማኒቴርያን አትላስ' ቀጣዮቹን ነጥቦች አስቀምጧል። ዳሰሳው ከስድስት ሚሊዮን ሰዎች ምን ያህሉ በምን ሁኔታ እንዳሉ ነው የሚያሳየው።
- አንድ ሦስተኛው በኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ባሉ አካባቢዎች ይኖራሉ።
- አንድ ሦስተኛው በኤርትራ ወታደሮች ቁጥጥር ሥር ባሉ ቦታዎች ይኖራሉ። የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አጋር ቢሆኑም ከሰብዓዊ እርዳታ ተቋሞች ጋር አይተባበሩም።
- 1.5 ሚሊዮን ሰዎች በትግራይ ገጠራማና በሽምቅ ተዋጊዎች ቁጥጥር ሥር ባሉ አካባቢዎች ይኖራሉ። እርዳታ ሰጪዎች ወደ እነዚህ አካባቢዎች አይሄዱም። የስልክ መስመርም ተቆርጧል።
የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የትግራይ የሽምቅ ተዋጊዎች እንቅስቃሴ "ውስን" እንደሆነ ገልጾ፤ በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር እንደሚሆን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ የሰብዓዊ ቀውሱ እየተባባሰ ይሄዳል ይላል። ጥያቄው ቀውሱ በምን ያህል ፍጥነት የት ድረስ ይስፋፋል? የሚለው ነው።
የአይፒሲ ሪፖርት ላይ "የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ ሪፖርት እውቅና አልሰጠም" ተብሏል።
ይህ ማስጠንቀቂያ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት "ረሃብ አለ" መባሉን ማጣጣላቸው አይቀርም።
ለዚህም እንደ መከራከሪያ የሚቀርበው፤ ሁኔታው ደረጃ አምስት የሚባለው (catastrophe) ላይ እንደሚገኝና ይህም በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የሚስተዋል መሆኑን ነው።
በየትኛው የትግራይ ክፍል በደረጃ አምስት ላይ የሚገኙ ሰዎች 20 በመቶ እንዳልደረሱ በመጥቀስም፤ መንግሥት ረሃብ ተከስቷል ማለት እንደማይቻል ይከራከራል።
የጨለማ እርሻ
የዩኤስኤድ ኃላፊ ሰማንታ ፓወር "የኢትዮጵያ መንግሥት ነገሮችን ግልጽ ላለማድረግ እየሞከረ ነው" ብለው ተችተዋል።
ክረምት ቢቃረብም የትግራይ አርሶ አደሮች ግን በአግባቡ ማረስ አለመቻላቸው ሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎችን አሳስቧል።
የጋንት ዩኒቨርስቲ በክልሉ እስካለፈው ዓመት ድረስ የግብርና ፕሮጀክት ይሠራ ነበር። ዘንድሮ ግን የትግራይ መሬቶች ላይ የሚያርስ ሰው አላስተዋሉም።
አርሶ አደሮች በሬ፣ ማዳበሪያና ሌላም ለእርሻ የሚያስፈልግ ቁሳቁስ የላቸውም።
ከዚህም በላይ የሚያፈራው ደግሞ የወታደሮች ማስፈራሪያ ነው። "አታርሱም፤ አታጭዱም፤ አለበለዚያ እንቀጣችኋላን" የሚል ዛቻ አርሶ አደሮች ይደርስባቸዋል።
በአንዳንድ ገጠራማ አካባቢዎች አርሶ አደሮች ጠዋት ላይ ወታደሮች ሳይደርሱባቸው በውድቅት ሌሊት ተነስተው እያረሱ ነው።
ወታደሮች እነሱ ወዳሉበት ከተቃረቡ መረጃ የሚያቀብል ሰው ይመደባል።
በዚህ ዓመት ካልታረሰ በትግራይ ያለ በርካታ ሕዝብ ለረሃብ ይጋለጣሉ ወይም ሕይወታቸው እርዳታ ላይ የተመሠረተ ይሆናል።
በትግራይ ሰው ሠራሽ ረሃብ አለ። ድርቅ የለም። አምና አስጊ የነበረው የአንበጣ ወረርሽኝም ተወግዷል።
ጦርነቱ ከመነሳቱ ከሰባት ወራት በፊት ክልሉ "አስተማማኝ የምግብ አቅርቦት ያለበት" ተብሎ ነበር።
የምግብ እርዳታ መዘረፍ
ጦርነቱ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን አቋርጧል። ባንክ ተዘግቷል። የመንግሥት የአደጋ ጊዜ ምላስ ሰጪ ሥርዓትንም አስተጓጉሏል።
የትግራይ ለም መሬቶች በአማራ ክልል ኃይሎች ተይዘዋል። የትግራይ ተወላጆች በመሬታቸው እንዳይጠቀሙ ከመታገዳቸው በተጨማሪ ከፍተኛ የሥራ እድል ያለበት ወቅትም አልፏል።
የኤርትራ ወታደሮች በዝርፊያ እንዲሁም ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር በመሆን ሰብል በማቃጠል፣ የጤና ተቋም በማውደም እና አርሶ አደሮች እንዳያርሱ በማድረግ ተከሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት 22,000 የመደፈር ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ድጋፍ ይሻሉ ብሏል። ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ይደርስብናል በሚል ስጋት ስለሚደበቁ ምግብ ማግኘት አይችሉም።
የረድዔት ድርጅቶች በአፋጣኝ እርዳታ መስጠት አልቻሉም። ለዚህም ምክንያቱ የደኅንነት ስጋት እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት የጣለው የቢሮክራሲ መሰናክል ነው።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፤ 2.8 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ ደርሷቸዋል። ሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎች ይህንን ቁጥር በቅርበት ሲያዩት፤ አብዛኞቹ ነዋሪዎች አንድ ጊዜ ብቻ እርዳታ ያገኙ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
ይህ የአንድ ዙር እርዳታ 30 ኪሎ ዱቄት ሊሆን ይችላል። አንድን ቤተሰብ ለ10 ቀናት ይመግባል።
ሁለተኛ ዙር እርዳታ ያገኙት እድለኞች ናቸው።
የእርዳታ ምግብና ቁሳቁስ የጫኑ መኪኖች በወታደሮች እንደሚዘረፉ በተደጋጋሚ ሪፖርት ተደርጓል።
ገለልተኛ አካሎች እንደሚሉት እርዳታ ከሚሹ 5.2 ሚሊዮን ሰዎች ድጋፍ ያገኙት 13 በመቶው ብቻ ናቸው።
በተጨማሪም ሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎች ተገድለዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ወደ ገጠራማ አካባቢዎች የሚሰማሩ እርዳታ ሰጪዎች እንዳይጓዙ አግዷል። ይህም እርዳታ ሰጪዎቹ የሽምቅ ተዋጊዎቹን ይረዳሉ በሚል ነው።
ባለሥልጣኖች እንደሚሉት የእርዳታ ቁሳቁስ እየተዘረፈ ያለው በሁሉም ወገን ባሉ የግጭቱ ተሳታፊዎች ነው።
ሆኖም ግን የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ወር 129 ጊዜ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች እንዲሁም ሚሊሻው "የእርዳታ አቅርቦትን አግደዋል" ይላል።
የትግራይ መከላከያ ሠራዊት እርዳታ ያገተው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነም የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።
የዩኤስኤድ ኃላፊ ሰማንታ ፓወር ሁኔታውን የገለጹት "እስካሁን ካያችሁት ሰብዓዊ ቀውስ የከፋው ነው" በማለት ነበር።
የተኩስ አቁም ጥሪ
የኖርዌጅያን ሬፍዩጂ ካውንስል ኃላፊ ጃን ኢግላንድ ከሁሉም ነገር ቅድሚያ የሚሰጠው "ረሃብን ለመከላከል የተኩስ አቁም ማድረግ" ነው ይላሉ።
ይህ ማንኛውንም ግጭት ማቆም፣ ንጹሀንን ከመደፈርና ከሌላም የመብት ጥሰት መታደግ እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ያካትታል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ፤ በቅርቡ የሚካሄድ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ድል እንደሚያስገኝ ተናግረዋል። ተኩስ አይቆምም ማለት ነው።
የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ መጠየቁን በተመለከተ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የባይደንን አስተዳደር "ግጭትና አለመረጋጋትን እያባባሰ ነው" ሲል ከሷል።
ህወሓት ሐሙስ እለት እርዳታ ተቀብሎ ለማከፋፈል ዝግጁ እንደሆነ ተናግሯል። ስለ ተኩስ አቁም ግን ምንም አላለም።
"አስከሬን እስክንቆጥር መጠበቅ የለብንም"
እርዳታ ሰጪዎች በግጭት በሚናጡ አካባቢዎች ድጋፍ ለማድረግ በሁለቱም ወገን ያሉ አካሎችን ትብብር ይሻሉ። በትግራይ ግን ይህ የሚሆን አይመስልም።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሽምቅ ተዋጊዎቹ "አሸባሪ" ናቸው በሚል ከነሱ ጋር ማንኛውም አይነት ትብብር እንዳይደረግ ማገዱ አንድ ምክንያት ነው። ትብብሩ የሰዎችን ሕይወት ለማዳን ያለመም ቢሆን።
በትግራይ የእርዳታ ሰጪዎች ቁጥር ቢጨምርም ጉልህ ለውጥ ለማምጣት ግን ገና ነው።
ከጦርነቱ በፊት እርዳታ የሚሰጥባቸው መሠረተ ልማቶች ፈራርሰዋል።
አሁን ካለው በላይ እርዳታ ያሻል። አሜሪካ እርዳታ ሰጪዎችን ለማስተባበር በማሰብ ተጨማሪ የ181 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጻለች።
ከዚህ ባሻገር በአማራ እና በአፋር ክልሎች የምግብ ክምችት በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ይገኛል። ይህ የጦርነቱ እንዲሁም የአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስ ውጤት ነው።
በሱዳንም ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደሚከሰት ተፈርቷል።
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የሚያስፈልገውን እርምጃ አልወሰደም። ከሦስት ዓመት በፊት እንዲህ አይነት ቀውሶች ሲገጥሙ የሚተገበር መርህ ወጥቶ ነበር።
ጦርነቱ ከተነሳ ከሰባት ወራት በኋላም የጸጥታው ምክር ቤት ለሕዝብ ይፋ የሆነ ውይይት አላደረገም። የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ግን የዓለማችን አስከፊው ሰብዓዊ ቀውስ ሆኗል።
የውሳኔ ሐሳብ (ሪዞሉሽን) 2417፤ የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ እርዳታን በሚያስጓጉሉ ግለሰቦችና ተቋሞች ላይ ማዕቀብ እንዲጥል ሥልጣን ሰጥቶታል።
ረሃብን እንደ ጦርነት መሣሪያ መጠቀም የጦር ወንጀል እንደሆነም ተደንግጓል።
የቡድን 7 አገራት ከውይይታቸው በኋላ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲሰጥ እንዲተባበሩ የማድረግ ጫናን ያበረታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ጄፍ ፌልትማን "ትግራይ ውስጥ ሰው ሠራሽ ረሃብ አለ ብለን ለማወጅ አስከሬን እስክንቆጥር መጠበቅ የለብንም" ብለዋል።
*የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አሌክስ ደዋል በአሜሪካው ተፍትስ ዩኒቨርስቲ በሚገኘው የፍሌቸር የሕግ እና ዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት ውስጥ የወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ናቸው። ኢትዮጵያን እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ አገራትን በሚዳስሱ የትንተና ጽሑፎቻቸው ይታወቃሉ።