የአሜሪካ ሴኔት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ የውሳኔ ሐሳብ አሳለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ሴኔት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ሁኔታ በማስመልከት የውሳኔ ሐሳብ ማሳለፉ ተገለጸ።
በትግራይ ክልል ባለው ግጭት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ህወሓት እና ሌሎች የግጭቱ ተሳታፊዎች ግጭቱን እንዲያቆሙ፣ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንዲፈቀድ ጠይቋል።
እንዲሁም ግጭቱን ተከትሎ ተዓማኒ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲመረመር ትብብር ያድርጉ ሲል ሴኔቱ የውሳኔ ሐሳብ አስተላልፏል።
የውሳኔ ሃሳቡ ለሴኔቱ የቀረበው መቼ ነበር?
ይህን የውሳኔ ሐሳብ ለሴኔቱ ያቀረቡት የሜሪላንድ ግዛት ዲሞክራቱ ሴናተር ቤንጃሚን ኤል ካርዲን ናቸው። ሴናተሩ እስካሁን ቢያንስ የ13 ሴናተሮችን ድጋፍ በማግኘት ምክረ ሐሳቡ ለሴኔቱ የቀረበው እአአ መጋቢት 9/2021 ነበር።
ቀደም ሲል ቀርቦ በነበረው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።
ሴኔቱ ምን አለ?
ሴኔቱ በመግቢያው ላይ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ወዳጅነት ዘመናትን የተሻገር መሆኑን አትቷል። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት አገር መሆኑን አስታውሶ፤ በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ግጭቱ እንዴት እንደተጀመረ ያስረዳል።
ከግጭቱ መከሰት በኋላ የፌደራሉ መንግሥት የውጭ አካላት የተደራደሩን ጥያቄ አልቀበለውም ማለቱን አስታውሶ ግጭት ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውን፣ ብዙ መልክ ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በበርካታ አካላት ሪፖርት ስለመደረጋቸው በዝርዝር አትቷል።
የሴኔቱ የውሳኔ ሃሳብ ምን ይላል?
ምክር ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ ሐሳብ ላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 10 ነጥቦችን ዝርዝሯል።
በመጀሪያ ሴኔቱ በትግራይ ክልል ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል። በንሑሃን ዜጎች ላይ የሚደርስ ጥቃት በጽኑ ይወገዛል ብሏል።
በሴኔቱ የውሳኔ ሃሳብ ላይ የቀረበው ሦስተኛው ሃሳብ ደግሞ፤ የኤርትራ ጦር በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ እንዲያስወጣ ይጠይቃል።
ጨምሮም በትግራይም ሆነ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በኤርትራ ሠራዊትም ሆነ በየትኛውም አካል የተፈጸሙ ማናቸውም አይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ግድያዎች፣ ዘረፋዎች፣ የመድፈር ወንጀሎች በጽኑ ይወገዛሉ ብሏል።
ሴኔቱ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የፖለቲካ ውጥረቱ ወደ ወታደራዊ ግጭት መግባቱን ተቀባይነት የለውም ብሏል።
በመላው ትግራይ የኤሌክትሪክ፣ የባንክ፣ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት በአፋጣኝ እና ሙሉ በሙሉ መመለስ አለባቸው ብሏል።
ሴኔቱ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ይጠበቅበታል ያለውን ሦስት ነጥቦች ዘርዝሯል።
እነዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ለአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንክ እና ለዓለም የምግብ ፕሮግራም ቃል በገባው መሠረት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ለማሻሻል ተጨባጭ እርምጃዎችን ይውሰድ ብሏል። የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙትን ተጠያቂ ማድረግ ይኖርበታልም ብሏል።
በቁጥጥር ሥር የሚውሉ የህወሓት አባላትን በተመለከተም የኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፍ ሕጎች መከበር አለባቸው ብሏል ሴኔቱ።
የኤርትራ ጦር በአስቸኳይ እና ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ እንዲወጣት የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲጠይቅ ሴኔቱ ጠይቋል።
በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ደጋፊዎች፣ ማኅበራዊ አንቂዎች እንዲሁም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ተጠቅምው የታሰሩ ጋዜጠኞች በብሔራቸው፣ በሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም እና የፖለቲካ ወገንተኝነታቸው ሳይለዩ ከእስር ይለቀቁ ጠይቋል።
በመላው አገሪቱ ተዓማኒነት ያለው እና ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድም ጠይቋል።
ሴኔቱ በተጨማሪም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ ግጭት እንዲያቆሙ፣ ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት የፖለቲካ መፍትሄ እንዲሰጥ፣ በዓለም አቀፍ ሕግጋቶች እንዲገዙ፣ በንሑሃን ዜጎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ተግባራት እንዲቆጠቡ ጠይቋል።
ሴኔቱ በመጨረሻ ምክረ ሃሳቡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፣ የገንዘብ ሚንስትር፣ የዩኤስኤይድ አስተዳደሪ ከሌሎች የአሜሪካ የፌደራል መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት እና ህወሓት ጋር በመገናኘት ግጭት እንዲቆም፣ የኤርትራ ጦር እንዲወጣ፣ የሰብዓዊ ቀውስ መፍትሄ እንዲሰጡ ጠይቋል።
ሴኔቱ የአሜሪካ መንግሥት ፌደራል አካላት የዲፕሎማሲ፣ የልማት እና የሕግ አማራጮችን በመጠቀም ተጨማሪ ብሔር ተኮር የሆኑ ግጭቶች እንዳይከሰቱ እና በኢትዮጵያ መድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲያብብ ጠይቋል።
ሴኔቱ በመጨረሻም የአሜሪካ መንግሥት ከዓለም አቀፍ አገር አገራት እና የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የቅርብ ትስስር በመፍጠር በትግራይ እና በተቀረበው የአገሪቷ ክፍል ለሚከሰቱ ግጭቶች መፍትሄ እንዲሰጡ አሳስቧል።
የሴኔት ሪዞሉሽን (የውሳኔ ሐሳብ) ምንድነው?
የሴኔት የውሳኔ ሐሳብ የሕግ ተፈጻሚነት የላቸውም። ምክረ ሐሳቦች በአንድ ጉዳይ ላይ የሴኔቱ አባላት የጋራ አቋምን የሚያንጸባርቁባቸው ናቸው።
በትግራይ ክልል ወታደራዊ ግጭት ከተከሰተ በኋላ የአሜሪካ መንግሥት አሁን ሴኔቱ ካሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ አቋም ሲያንጸባርቅ የቆየ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋርም በተደጋጋሚ ሲወያይበት መቆየቱ ይታወሳል።
በተጨማሪም አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉላትን አንጋፋ ዲፕሎማት ሰይማ ባለፉት ሳምንታት በአካባቢው ጉብኝት አድርገዋል።












