የኢትዮጵያ ወታደሮች 'የህወሓት ተዋጊዎችን ፍለጋ ሆስፒታል መፈተሻቸው' ተነገረ

የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ባለፈው እሁድ ትግራይ አክሱም ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ ሆስፒታል ገብተው ፍተሻ ማድረጋቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ።

ወታደሮቹ በታሪካዊቷ ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው ሆስፒታል የገቡት የህወሓት ተዋጊ አባላትን ለመፈለግ እንደሆነ የዜና ወኪሉ የጠቀሳቸው ሐኪሞች ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ ውስጥ የሚሰሩና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጤና ባለሙያዎች ነገሩኝ ብሎ ኤኤፍፒ እንደዘገበው፤ ወታደሮቹ ዶክተሮች፣ ነርሶችና ቁስለኛ ታካሚዎች ላይ መሳሪያ በመደገን ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበር።

ኤኤፍፒ ዋቢ ያደረጋቸው የጤና ባለሙያዎች ወታደሮቹ "ታካሚዎቹ የተሰጣቸውን ጉሉኮስ እንደነቀሉና ቁስላቸው የተሸፈነበትን ጨርቅ አንስተዋል" ብለዋል። ወታደሮቹ የጦር መሳሪያ እንደደቀኑባቸው የህክምና ባለሙያዎቹ ጨምረው ተናግረዋል።

ሆስፒታሉን የሚደግፈው የህክምና በጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ኤምኤስኤፍ ክስተቱ ማጋጠሙን አረጋግጧል።

ኤምኤስኤፍ ባወጣው መግለጫ ላይ እንደጠቀሰው ወታደሮቹ በሆስፒታሉ ውስጥ በሚገኙ ክፍሎች ውስጥ እየተዘዋወሩ "አስታማሚዎችንና የጤና ሠራተኞችን አስፈራርተዋል" ብሏል።

አክሎም "የህክምና ተልዕኮዎችን ገለልተኝነት በሚጥስ ሁኔታ በተደጋጋሚ የሚከሰቱት የታጠቁ ቡድኖች ተደጋጋሚ ድርጊት በእጅጉ ያሰስበናል" ሲልም ኤምኤስኤፍ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

የህክምና በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከወራት በፊት ባወጣው ሪፖርት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው የህክምና ተቋማት ሆን ተብለው ጉዳት እንዲደርስባቸው መደረጉን ገልጾ ነበር።

ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የህወሓት ኃይሎች ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ በክልሉ ውስጥ ወታደራዊ ዘመቻ መካሄዱ ይታወሳል።

አሁንም የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአንዳንድ አካባቢዎች ውጊያዎች የሚካሄዱ ሲሆን፤ ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ የሚገመት ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ በአገር ውስጥና በጎረቤት አገር ሱዳን ውስጥ ተፈናቅለው ይገኛሉ።

ግጭቱ በተካሄደባቸው ስፍራዎች የኤርትራ ወታደሮችን ጨምሮ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች የተለያዩ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ማውጣታቸው ይታወሳል።