የአፍሪካ-ፈረንሳይ ስብሰባ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሦስት አገራት የብድር እፎይታ ሃሳብ በማቅረብ ተጠናቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ላለፉት ጥቂት ቀናት በፓሪስ ሲካሄድ የቆየው የፈረንሳይ-አፍሪካ ስብሰባ ብድር መክፈል ለተሳናቸው የአፍሪካ አገራት የብድር እፎይታ ሃሳብ በማቅረብ ተጠናቀቀ።
የቀረበው ምክረ ሃሳብ ለኢትዮጵያ፣ ቻድ እና ዛምቢያ የብድር እፎይታ እንዲደረገ የሚጠይቅ ሲሆን ይህም ምክረ ሃሳብ በቀጣይ ወር ለጂ7 አገራት ይቀርባል ተብሏል።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ባለጸጋ አገራት ደሃ አገራት የሚጠበቅባቸውን ብድር የሚከፍሉበትን ጊዜ ላልተወሰነ ጊዜ ለማራዘም ተስማምተው ነበር።
የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ስምምነት ከተደረሰላቸው አገራት መካከል 40 ያክሉ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ናቸው።
በስብሰባው ላይ ከ20 በላይ የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ የአውሮፓ አገራት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ሕብረት ልዑካን እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ (አይኤምኤፍ) ዳይሬክተር ተሳታፊ ሆነዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በስብሰባው መጠናቀቂያ ላይ የስብሰባው ተሳታፊዎች በኮቪድ-19 የተጎዳውን የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ መልሶ እንዲያንሰራራ ተጨማሪ 100 ቢሊዮን ዶላር ለማፈላለግ ተስማምተዋል ስለማለታቸው ኤፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ከዚህ መካከል አይኤምኤፍ የአፍሪካ አገራት ምርት ወደ አገራቸው እንዲያስገቡ እንዲረዳቸው 33 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል።
ይህ ድጋፍ አገራቱ ባላቸው ሃብት ላይ ትኩረት በማድረግ በኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት የተጎዳ ምጣኔ ሃብታቸው እንዲያንሰራራ ትኩረት እንዲያደርጉ ያስችላል ተብሏል።
ይህ የፈረንሳይ-አፍሪካ ውይይት የአፍሪካ አገራት የኮቪድ-19 ክትባት ስለሚያገኙበት አማራጭ ላይም መወያየቱን ሬውተርስ ዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንደ ኤፒ ዘገባ ከሆነ የውይይቱ ተሳታፊዎች የአፍሪካ አገራት ለዜጎቻቸው የኮቪድ-19 ክትባቶችን በራሳቸው በስፋት ማምረት እንዲቻላቸው ከአእምሮ መብት ጥበቃ ጋር የተያያዙ ክልከላዎች መላላት አለባቸው በሚል ተስማምተዋል ብለዋል ማክሮን።
"የአፍሪካ አዲስ ስምምነት" የሚል መጠሪያ የሰጡት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ የአፍሪካ አገራትን ለመደገፍ 100 ቢሊዮን ዶላር በቂ አለመሆኑን ገልጸው፤ "በቀጣይ ዋነኛ ሥራችን የሚሆነው ሌሎች አገራት እንደ ፈረንሳይ ተመሳሳይ ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ማግባባት ነው፤ ይህም ከዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ይጀምራል" ብለዋል።
የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂኦርጂቫ አይኤምኤፍ ተጨማሪ 33 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያቀርብ ይፋ አድርገው፤ ከኮሮናቫይረስ ስርጭት በኋላ የአፍሪካ አገራት እንደተቀረው ዓለም በፍጥነት ከገቡበት የምጣኔ ሃብት አጣብቂኝ ፈጥነው መውጣት አለመቻላቸው አሳሳቢ ነው ብለዋል።
የተቀረው ዓለም በአማካይ የምጣኔ ሃብት እድገታቸው 6 በመቶ ሲሆን በአፍሪካ አገራት ግን የምጣኔ ሃብት እድገቱ 3.2 በመቶ ብቻ መሆኑን ዳይሬከተሯ ገልጸዋል።












