ኢትዮጵያ 1 ቢሊዮን ችግኞች ለጎረቤት አገራት ልታድል ነው

ችግኝ

የፎቶው ባለመብት, MICHAEL TEWELDE

'ኢትዮጵያን እናልብሳት' በሚል መርሃ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊየን ችግኝ የሚተከል ሲሆን አንድ ቢሊየን ችግኝ ደግሞ ለጎረቤት አገራት ይሰጣል ተባለ።

በመርሃ ግብሩ መሠረት ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኬንያ ለመድረስ መታቀዱን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሃሰን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ከትናንት በስቲያ ይህን የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ባስጀምሩበት ወቅት የአካባቢ ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ የወጣው የአራት ዓመት እቅድ አካል መሆኑን ገልጸው ነበር።

"ለመላው ኢትዮጵያውያን "ኢትዮጵያን እናልብሳት" ብዬ ጥሪ አቀርባለሁ" ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ጽፈው ነበር።

የግብር ሚንስትሩ ዕቅዱ በኢትዮጵያ አነሳሽነት የሚተገበር መሆኑን ጠቅሰው "ኢትዮጵያ ናት ሃሳቡን ያነሳቸው እንጂ ሃገራቱ ይህ ይሰጠን ብለው አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የጎረቤት አገራትን ማካተቱ የዲፕሎማሲ አካል መሆኑን አስታውሰው፤ "የባህል ዲሎማሲም ዓይነት ነው። ከሌላ ስጦታም በላይ ተመሳሳይ ሥራ አብሮ ቢሰራ ትልቅ መነቃቃት ይፈጥራል በሚል ነው" ሲሉ አስረድተዋል።

መርሃ ግበሩ ከጅቡቲ በመጀመር ወደ ሌሎች አገራት እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ለጎረቤት አገራት ከሚሰጡት አንድ ቢሊየን ችግኞች መካከል ወደ 780 ሚሊዮን የሚሆኑት ችግኞች አይነታቸውም ሆነ የሚፈልጉት የአየር ጸባይ የተለየ መሆኑን እና በቅርብም ማከፋፈል እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

የግብርና ሚንስትሩ ኡመር ሃሰን በአገር አቅፍ ደረጃ የሚተከሉት 6 ቢሊዮን ችግኞች በክልል ከተሞች እና በከተማ ዳርቻ አካባቢ ባሉት ቦታዎች እንደሚሆን ተናግረው፤ የክልሎች የችግኞች ድርሻ የሚወሰነው በዝግጅታቸው ልክ ይሆናል ብለዋል።

ደን ለመፍጠር ከሚያስችሉ ችግኞች ጎን ለጎን በአጭር ጊዜ ጥቅም የሚሰጡ እንደ አቮካዶ እና ፓፓዬ ያሉትም ይተከላሉ ብለዋል።

"ቁጥሩ ከፍ ሲል ሰዉ በደን መልክ ብቻ ስለሚያስብ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ለሌላ ጥቅም ሲያውለው የነበረውን እና ከ3-5 ዓመት እየተከለ የሚጠቀምበትን ማለት ነው። ፍሬውን ሸጦ የሚጠቀምበት ዓይነት ዝርያዎችንም እንዲኖሩ ተደርጎ ነው የተዘጋጀው" ሲሉ ገልጸዋል።

እስካሁን በአገር አቀፍ ደረጃ ስለተደረጉ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ውጤታማነት አስመልክተውም "ቀደም ሲል በብሔራዊ ደረጃ ዕድገቱ በጣም የወረደ ነበር። ከ65-72 በመቶ አካባቢ ነበር። አሁን ግን ያሉትን ሁለት ዓመታት አማካይ ስናወጣ አምና ከተተከለው 5.9 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ 87 በመቶ ያህሉ አጸዳደቁ ጥሩ እንደሆነ ታይቷል" ሲሉ መልሰዋል።