የቻይናን እገዳ ተከትሎ የቢትኮይን ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ አሽቆለቆለ

ቢትኮይን

የፎቶው ባለመብት, NURPHOTO

ቻይና በክሪፕቶከረንሲ ላይ የጣለችውን እገዳ ተከትሎ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ከ34 ሺህ ዶላር በታች አሸቆለቆለ።

የቢትኮይን ዋጋው በዚህ ደረጃ ሲያሽቆለቁል ከሦስት ወራት በኋላ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ቤጂንግ ማክሰኞ ዕለት የገንዘብ ተቋማት እና የክፍያ ኩባንያዎች ከክሪፕቶከረንሲ ግብይቶች ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን እንዳይሰጡ አግዳለች።

ቻይና ባለሃብቶችንም በክሪፕቶከረንሲ ከሚያደርጉት የንግድ እንቅስቃሴ እራሳቸውን እንዲቆጥቡ አሳስባለች።

ክሪፕቶከረንሲን ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ ብለን በግርድፉ ልንጠራው እንችላለን። ቢትኮይን ደግሞ በስፋት ተቀባይነት ካገኙት ዲጂታል ገንዘቦች መካከል አንዱ ነው።

ከቀናት በፊት የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ ለማመርታቸው መኪኖች ቢትኮይንን በክፍያ መልክ አልቀበልም ማለቱን ተከትሎ የቢትኮይን ዋጋ 10 በመቶ ቀንሶ ነበር።

ሰኞ ዕለት ደግሞ የክሪፕቶከረንሲው ዋጋ በ22 በመቶ ቀንሷል። ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 6 ሺህ ዶላር ገደማ ዋጋውን ወርዷል።

እንደ ኢተርዩም እና ዶጅኮይን ያሉ ሌሎች ዲጂታል ገንዘቦች ደግሞ በቅደም ተከተል የ 25 በመቶ እና 29 በመቶ ቅናሽ አስመዝግበዋል።

በተመሳሳይ ወቅት የቴስላ አክሲዮን በዎል ስትሪት ያለው ዋጋ ከሦስት በመቶ በላይ የቀነሰ ሲሆን የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ከቢትኮይን ጋር በመያያዙ ሊሆን ይችላል ተብሏል።

በኤሎን መስክ ባለቤትነት የተያዘው ኩባንያ እስከ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ክሪፕቶከረንሲ በእጁ ይገኛል።

የቤጂንግ እገዳ

ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት ሲባል እአአ ከ 2019 ጀምሮ በቻይና የክሪፕቶከረንሲ ንግድ ሕገ-ወጥ ነው።

ቤጂንግን እያሳሰባት ያለው ሰዎች አሁንም እንደ ቢትኮይን ባሉ ገንዘቦች በድረ-ገጽ መገበያየት መቀጠላቸው ነው።

ማክሰኞ ዕለት በመንግሥት የሚደገፉ ሦስት ድርጅቶች በማህበራዊ ድር አምባዎች ላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ሸማቾች በክሪፕቶከረንሲ ግብይቶች ምንም ዓይነት ኪሳራ ቢያጋጥማቸው ጥበቃ አይኖራቸውም ብለዋል።

በቅርብ ጊዜ በክሪፕቶ ከረንሲ ዋጋዎች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ መዋዠቅ የሰዎችን የንብረት ደህንነት በእጅጉ የሚጥስ እና "መደበኛውን የኢኮኖሚ እና የገንዘብ ስርዓት" እያወከ ነው ብለዋል።

የቴስላ ማፈግፈግ

የቴስላው አለቃ ኤሎን መስክ ባለፈው መጋቢት ወር ባልተጠበቀ ሁኔታ የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ደንበኞቹ ቢትኮይን በመጠቀም መኪናዎችን መግዛት ይችላሉ ሲል አስታውቆ ነበር።

ባለፈው ሳምንት መስክ ሃሳቡን በመሰረዝ በከባቢያዊ ላይ በሚያደርሰው ችግር ምክንያት ቢትኮይን በመጠቀም የተሽከርካሪ ግዥዎችን መፈጸም አይቻልም ሲል አገደ።

የቢትኮይንን ስርዓት የሚያሳልጡ ኮምፒውተሮች ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይልን ይጠቀማሉ።ብዙውን ጊዜ ኃይሉን ከነዳጅ በተለይም ከከሰል በሚመነጨው ኤሌክትሪክ ላይ መሠረት ያደረገ ነው።

"ቢትኮይንን ለመጠቀም እና ለግብይት ነዳጅ በተለይም የድንጋይ ከሰል አጠቃቀም በፍጥነት መጨመሩ ያሳስበናል" ሲል አስፍሯል።

"ክሪፕቶከረንሲ ጥሩ ሀሳብ ነው ... ይህ ግን አካባቢ ላይ ከፍተኛ ዋጋ በማስከተል መሆን የለበትም" ብሏል መስክ።

ኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ በእጁ የሚገኘውን ቢትኮይን ለመሸጥ እንዳላሰበ አስታውቋል። አሠራሩ ይበልጥ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ወደ መጠቀሙ ከተሸጋገረ በኋላ ለመጠቀም የታሰበ ነው ሲል አስታውቋል።

ዲጂታል ገንዘብን በቻይና መገበያየት ባይችልም ከ 75 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለማችን የቢትኮይን ማይኒንግ (አዲስ ቢትኮይን ወደ ገበያ ሚገባበት ስርዓት ማለት ነው) በቻይና ይፈጸማል።