ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹ የደኅንነት ስጋት እንዳለባቸው በማስረጃ እንዲያረጋገጥ ተጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዐቃቤ ሕግ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር በተከሰሱ ሰዎች ላይ "የማቀርባቸው ምስክሮች ቃላቸውን በይፋ ለመስጠት ስጋት አለባቸው" ማለቱን ተከትሎ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ በምስክሮቹ ላይ ያለውን ስጋት በማስረጃ እንዲቀርብ ጠየቀ።
ዐቃቤ ሕግ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ የጠራኋቸው ምስክሮቼ የደኅንነት ስጋት ስላለባቸው በዝግ ችሎት እና ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነታቸውን ይስጡ በማለት ሲከራከር መቆየቱ ይታወሳል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ በምስክሮች ላይ ሊኖር የሚችልን ስጋት በማስረጃ ተደግፎ ዐቃቤ ሕግ ለታችኛው ፍርድ ቤት ማለትም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ወስኗል።
በዚህ መሠረት ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ናቸው ብሎ የቆጠራቸው 146 ሰዎች ቃላቸውን በግልጽ ችሎት በመስጠታቸው ሊያጋጥማቸው ስለሚችለው የደኅንነት ስጋት በማስረጃ አስደግፎ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀርባል ማለት ነው።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ከዚህ ቀደም በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር ከተከሰሱ ሰዎች ጋር በተያያዘ፤ "የዐቃቤ ሕግ መስክሮች በግልጽ ችሎት ቃላቸውን ይስጡ" ሲል የሰጠውን ብይን በመቃወም ነበር የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያለው።
የዐቃቤ ሕግ መስክሮች በግልጽ ችሎት አልያም ከመጋረጃ በስተጀርባ እና በዝግ ችሎት ቃላቸውን ይስጡ የሚለው ጉዳይ ዐቃቤ ሕግ እና የተከሳሽ ጠበቆችን ሲያከራክር ቆይቷል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀጣይ ዐቃቤ ሕግ በሚያቀርበውን ማስረጃ እንዲሁም በዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሾች/የተከሳሽ ጠበቆች መካከል የሚከናወነውን ክርክር መሠረት አድርጎ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የዐቃቤ ሕግ እና የተከሳሽ ጠበቆች ክርክር
ዐቃቤ ሕግ፤ ከዚህ ቀደም ምስክሮቼ "የደኅንነት ስጋት አለባቸው ወይስ የለባቸውም፤ እንዲሁም በዝግ ችሎት እና ከመጋረጃ ጀርባ መስክርነት ይስጡ የሚለውን ለመመርመር እና ውሳኔ ለመስጠት ፍርድ ቤት ስልጣን የለውም" ሲል ተከራክሯል።
ዐቃቤ ሕግ ይህን የመመርመር እና ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ያለው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ነው ሲል ተከራክሯል።
ይሁን እንጂ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ፤ ችሎቱ ክፍት ወይስ ዝግ ይሁን በሚለው እንዲሁም አንድ ምስክር ቃል መስጠት ያለበት በይፋ ነው ወይስ ከመጋረጃ በስተጀርባ በሚለው ላይ ውሳኔ መስጠት የሚችለው ፍርድ ቤቱ ነው ሲል ውስኗል።
በሌላ በኩል በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር የተከሰሱት ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና የአመራሮቹ ጠባቂዎች ናቸው፣ ብዙ ደጋፊዎች አሏቸው፣ ምስክሮቻችን በይፋ ቃላቸውን የሚሰጡ ከሆነ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል ሲል ዐቃቤ ሕግ ከዚህ በፊት ተከራክሯል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን የሚሰጡ ከሆነ የደንበኞቻቸውን በክፍት ችሎት የመዳኘት መብት የሚጋፋ ነው በማለት ሲከራከሩ ቆይተዋል።
የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን የሚሰጡ ከሆነ ደንበኞቻቸውን መስቀለኛ ጥያቄ ለመየቅ ይከብዳቸዋል ሲሉም ተከራክረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ጠበቆች ደንበኞቻቸው ላይ የቀረበው ክስ ከሰባት ዓመት እስራት እስከ በሞት የሚያስቀጣ ስለሆነ፤ መሰል ክስ የቀረበባቸው ተከሳሾች የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች "ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን ይስጡ ማለቱ ፍትሃዊ አይሆንም" ብለው ነበር።
በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር የተከሰሱ ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ናቸው ሲል ላቀረበው መከራከሪያ ጠበቆች በክስ መዝገቡ ሥር የተካተቱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ቁጥር ከሦስት አይዘልም ሲሉ ተከራክረው ነበር።
አቶ ጃዋር መሐመድና አብረዋቸው ፍርድ ቤት የቀረቡት ግለሰቦች ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በታዋቂው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ነበር ለእስር የተዳረጉት።
አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙት ተከሳሾች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።












