የኤርትራ ምጣኔ ሃብት ባለፉት 30 ዓመታት

ኤርትራ ገንዘብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤርትራ በ1992 ዓ.ም 52ኛ አፍሪካዊት አገር ስትሆን ዜጎቿና የነጻነት ጉዞዋን ሲከታተሉ የነበሩ ተንታኞች 'ኤርትራ በአጭር ጊዜ ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝገብ የአካባቢዋ ሞዴል ትሆናለች' የሚል ተስፋ ነበራቸው።

ከነጻነት በኋላ የነበሩ የጊዝያዊ አስተዳደሩ ስራ አስፈጻሚዎችም "ኤርትራን ሲንጋፑር እናደርጋታለን" ሲሉ ተናግረው ነበር።

አገሪቷ በ1994 ያጸደቀችው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በግብርና ኢንዳስትሪ፣ አሳና ጨው፣ የመሰረተ ልማቶች ግንባታ፣ ኤሌክትሪክና ውሃ ማስፋፋት፣ ትምህርት፣ ጤናና ሌሎች የማስፈጸም ተልእኮ ተሰጥቶት ስራ ተጀመረ።

ሰነዱ መግቢያ ላይ "ኤርትራ ከጦርነትና ግጭት፣ ከጭቆና አገዛዝ nጻ ወጥታ ወደ አዲስ ብልጽግናና ሰላም እየገባች ነው። ይህ በመስዋእትነት የተገኘው ሰላምና መረጋጋት ፈጣን ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እያሳየ ነው። በጦርነት የወደመው ምጣኔ ሃብትን ለመገንባትም ጥረት እየተደረገ ይገኛል" ይላል።

የአፍሪካ ፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪ ፕሮፌሰር መንግስትአብ ኪዳነ የኤርትራ መንግሥት በግል ባለሃብቶች የሚመራ የኢንቨስትመንትና ወደ ውጪ የሚላክ ምርት ትኩረት ያደረገ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ እንደነደፈ ያስታውሳሉ።

"መንግሥት የህግደፍ ኢኮኖሚ፣ የመንግሥት ኢኮኖሚ፣ የግል ኢንቨስትመንት ኢኮኖሚ በሚል ሦስት መንገድ የተገበረውን ፖሊሲ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለበት መንገድ እጁ ማስገባት ስለጀመረ ብዙ ርቀት ሳይጓዝ ነው የተደናቀፈው" ይላል።

በተዘበራረቀ አሰራር ምክንያት ህዝብ የመንግሥት የሆነው ንብረት ከፓርቲ ሃብት ለይቶ ማየት እንዳልቻለ የሚናገረው ፕሮፌሰር መንግስትአብ፤ "ለምሳሌ ህዝብ ማዕድን በመንግሥት ነው ወይስ በፓርቲ የሚተዳደረው የሚያውቀው ነገር አልነበረም" በማለት የአገሪቷ የምጣኔ ሃብት ስርአት የተዘበራረቀ መሆኑ ይናገራል።

በሳውዝ ባንክ ዩኒቨርሲቲ ለንደን ፕሮፌሰር የሆነው ጋይም ክብረአብ በበኩሉ፤ ህዝቡ፣ በመንግስት በኩል የነበረበትን አስተዳደራዊ ችግር "ልምድ እስኪያገኙ ድረስ ነው" እያለ ጊዜ ቢሰጠውም በጊዜ ማስተካከል ባለመቻሉ የአገሪቷ ምጣኔ ሃብትና ፖለቲካ ወደ ኋላ ቀርቷል ይላል።

በዚህ ምክንያት ብዙ በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ፍላጎት የነበራቸው ዜጎች እውቀታቸውና ገንዘባቸው ይዘው ከስደት ወደ አገራቸው ቢመለሱም፤ የግል ኢኮኖሚው ህጋዊ ግብር የማይከፍለው የፓርቲ ኢኮኖሚ ጋር መወዳደር ባለመቻሉ ቀስ በቀስ እንደከሰረ ያስረዳል።

ይህ አሰራር ማን ምን እንደሚያስተዳድር ስለማይታወቅ ለሙስና የተጋለጠ እንደሆነ የሚያነሳው ፕሮፌሰር መንግስትአብ፣ በፓርቲ የሚመራው የኢኮኖሚ ተቋም በኢንዳስትሪ፣ ግንባታ፣ ትራንስፖርት፣ መሰረታዊ ሸቀጦች ሳይቀር ስለሚሳተፍ የኢኮኖሚው መተላለፊያ በመቆጣጠር ነጋዴዎች እድል ስለነፈጋቸው ኢኮኖሚው በአግባቡ መራመድ አልቻለም ይላል።

"መንግሥትና ፓርቲ የውጭ ምንዛሪና ብድር ተቆጣጥረው የግል ኢንቨስትመንቱን አዳከሙት። በዚህ ላይ ወጣቱ በአገራዊ ግዳጅ ስለተጠመደ በግብርና እና የቀን ስራ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ሰራተኛ አጥተው ኢኮኖሚው እንዲወድቅ ሆኗል" በማለት ያስረዳል።

እንዲህም ሆኖ ዜጎች በንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ ያደርጉ ስለለነበረ በ1996 የአገሪቷ ኢኮኖሚ እስከ 6.7 በመቶ እድገት እንዳስመዘገበ ፕሮፌሰር ጋይም ይናገራል።

በፋይናንስ ሚኒስትር የኢኮኖሚ ኃላፊ የነበረው አቶ ክብሮም ዳፍላ በወቅቱ ከኤርትራ መገናኛ ብዙሃን ባደረገው ቆይታ እሱ ኃላፊነት ላይ በነበረበት ወቅት ያስተዳድረው የነበረው ተቋም 'ሂምቦል የውጭ ምንዛሪና ሃዋላ' ብቻ በአመት እስከ 80 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ ይመነዘር ነበር ብሏል።

በተጨማሪም በተመሳሳይ ንግድ ተሰማርተው የነበሩ ሌሎች የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ለመስጠት ፍቃድ የተሰጣቸው 29 ተቋማት እንደነበሩ ገልጿል።

የልብስ ማምረቻ ሠራተኛ

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትና ለ20 መታት የዘለቀው ውዝግብ

በአስተዳደራዊ ችግርና ጫና ለህግደፍ የንግድት ተቋማት ይሰጥ በነበረው ኢፍትሃዊ የግብርና ቀረጥ እፎይታ ሲያዘግም የነበረው ብቸኛ ኢኮኖሚ፣ ለሁለት አመታት በዘለቀው የኢትዮ ኤርትራ ግጭት ምክንያት ተንኮታኮተ።

ጦርነቱ ተከትሎ ላለፉት 18 አመታት በቀጠለው ውዝግብም አብዛኛው ዜጋ በብሄራዊ አገልግሎት እንዲጠመድ ስለሆነ እንደምንም ሲንቀሳቀስ የነበረው ኢኮኖሚ በጦርነት ታግቶ እንደቆመ ፕሮፌሰር ጋይም ይናገራል።

"የኤርትራ ብሄራዊ በጀት የሚመለከት ሆነ አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ሪፖርት ስለሌለ በጦርነቱ ምክንያት ምን ያክል ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንደደረሰ ባይገለጽም የነበረውን መባከኑን ግን ግልጽ ነው" ይላል።

የኤርትራ መንግሥት ባለስልጣናት ግን "በቅድሚያ የአገር ሉአላዊነት መረጋገጥ ስላለበት አገር ሳናስጠብቅ የውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ መነጋገር ጊዜው አይደለም" ሲሉ ቆይተዋል።

የመንግሥት ኢኮኖሚያዊ ቅርጽ ሁሉንም የኢኮኖሚ አማራጮች በመቆጣጠሩ ዲሞክራሲያዊ አሰራር እንዳይኖር አድርጓል የሚለው ፕሮፌሰር መንግስተአብ በበኩሉ፤ "ፓርቲው የራሱ ኢኮኖሚ ስለገነባ ከህዝብ ጋር የሚያስተሳስረው መንገድ አይኖረውም። ለዚህም እስከ ዛሬ ለህዝብ ጥያቄ ጆሮ አልሰጠም። ህዝቡም ድምጹን የሚሰጥበት እድል ስለሌለ በድምጹ ተቃውሞ ማሰማት አልቻለም" ይላል።

በዲሞክራሲያዊ አገር ፓርቲ ከአባላቶቹ በሚሰበስበው መዋጮ ነው የሚተዳደረው።

በኤርትራ ግን ህገ መንግሥታዊ ስርአት ስሌለለ አገሪቷን የሚያስተዳድር ፓርቲም አንድና አንድ ብቻ ስለሆነ፤ ህግደፍ የአገሪቷን ንብረት በሙሉ እያስተዳደረ ይገኛል።

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ያላደገበት አንድ ምክንያትም ዴሞክራሲያዊ የሆነ አሰራር አለመኖሩ ነው ሲል ፕሮፌሰር ጋይም ያስረዳል።

የቢሻ ማዕድን ማውጫ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የቢሻ ማዕድን ማውጫ

ማዕቀብ

ኤርትራ እኤአ በ2009 ከሶማልያ ጋር በተያያዘ፣ በ2011 ከጅቡቲ ጋር በነበራት አለመግባባት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክርቤት የመሳሪያ ግዢና የተወሰኑ ሰዎች ባንክ እንዳይንቀሳቀስ በማለት ማዕቀብ ጥሎባት ነበር።

መንግሥት 'መሬት ላይ የሌለ ነገር በመጠቀም ኤርትራን ለማዳከም የተወሰደ ተከታታይ የአሜሪካ መንግሥታት ሴራ ነው፤ ከኢትዮጵያ ጋር በነበረው ግጭት ምክንያት በማድረግ የአፍሪካን ቀንድ ለመቆጣጠር ያሴሩት ነው' ሲል ቅሬታው ይገልጽ ነበር።

በመጨረሻም ኤርትራና ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ሲፈርሙ ህዳር 14 2019 ላይ ማእቀቡ ተነሳ።

ሁለቱም አገራት ስምምነት ከፈረሙ በኋላ የተዘጉ ድንበሮች ሲከፈቱ የአገሪቷ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አሳይቶ ነበር።

ይሁን እንጂ ድንበሮቹ ምክንያቱ በውል ባይታወቅም ተመልሰው በመዘጋታቸው የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ዳግም ማሻቀቡን የኤርትራ ምንጮች ይገልጻሉ።

ፕሮፌሰር ጋይም ግን ከዚህ በፊት ኤርትራ ላይ የተደነገጉ ማዕቀቦች በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ጫና አሳድሯል የሚለው እምነት እንዳለው ተናግሯል።

በሌላ በኩል መንግሥት በ2015 ህገ ወጥ የውጭ ምንዛሬ ጭማሪ ለመቆጣጠር፤ የአገሪቷን ገንዘብ በመቀየር ሁሉንም በህዝብና ነጋዴዎች እጅ የነበረው ገንዘብ ባንክ እንዲገባ ካደረገ በኋላ ታላላቅ የንግድ ልውውጥ በባንክ እንዲከናወን ትእዛዝ አስተላለፈ።

ዜጎችም ከ5 ሺ ናቅፋ በላይ ከባንክ ማውጣት እንደማይችሉ የሚቆጣጠር ህግ ተግባራዊ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል። ይህም ምታኔ ሃብቱ እንዲዳከም ማድረጉ ፕሮፌሰሩ ያስረዳል።

የኤርትራ ህዝብ ለነጻነት ሲታገሉ የነበሩ ድርጅቶች በቻለው ሁሉ እርዳታ በማድረጉ ለድል በቅቷል የሚለው ፕሮፌሰር መንግስትአብ በጣልያን እና ሌሎች አገሮች በስደት የነበሩ እናቶች ከፍተኛ የሞራልና የኢኮኖሚ ድጋፍ አድርገዋል ይላል።

ከ1998 እስከ 2000 በነበረው የድንበር ግጭት ብዙ ህዝብ የአገሩን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ቦንድ በመግዛትና በጥሬ ገንዘብ በመለገስ ማገዙን የሚያነሳው ፕሮፌሰር መንግስትአብ 'አገሬ ሽልማቴ' በማለት እናቶች ሽልማታቸውን አበርክተዋል ሲል ያስታውሳል።

በተጨማሪም ከጦርነቱ በኋላም ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሳይመጣ በአንጻሩ ለውጥ ሲጠይቁ የነበሩት ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችና ጋዜጠኞች ያለ አግባብ ታስረው ይገኛሉ፤ እነዚህ እና ሌሎች ተያየዓዥ ምክንያቶች ተደማምረው የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት እንዲጎዳ አድርጓል ይላል።

በመሆኑም "ፖለቲካዊ ለውጥ ካልመጣ ኢኮኖሚያዊ እድገት የማይታሰብ ነው" ሲል ፕሮፌሰር ጋይም መሰረታዊ ማሻሻያ ለማድረግ የማክሮ ኢኮኖሚ መርሆዎችን ተመልሶ ማየት አስፈላጊ ነው ሲል ይመክራል።