ኤርትራ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናን ያልፈረመች ብቸኛዋ ሃገር ሆነች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአፍሪካ የምጣኔ ሃብት ኃያል ሃገር ባለቤት ናይጄሪያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ፈረመች። ይህም ኤርትራን ስምምነቱን ያልፈረመች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሃገር አድርጓታል።
የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ሙሃመዱ ቡሃሪ በኒጄር በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።
ነጻ የንግድ ቀጠናው ስምምነት ዓላማ በአባል ሃገራት መካከል በሚደረጉ የንግድ ልውውጦች ላይ ታሪፍን በማስቀረት አፍሪካውያን ሃገራት እርስ በእርሳቸው የንግድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ለማበረታታት ያሰበ ነው ተብሏል። ይህ ስምምነት ወደ ሥራ የሚገባበት ቀን ለጊዜው አልተወሰነም።
በአሁኑ ወቅት አፍሪካውን ሃገራት ምርት እና አገልግሎታቸውን እርስ በእርስ የሚነግዱት 16 በመቶ ብቻ ሲሆን አውሮፓውያን ሃገራት ግን ከሚያመርቱት ምርት እና አገልግሎት 65 በመቶ የሚሆነውን ለተቀረው አውሮፓ ሃገር ይሸጣሉ።
የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ተግባር ላይ ማዋል፤ እአአ በ2022 ላይ በአፍሪካ ሃገራት መካከል የሚደረገውን የንግድ ለውውጥ በ60 በመቶ ከፍ ያደርገዋል ሲል ግምቱን ያስቀምጣል።
በተጨማሪም ስምምነቱ በዓለማችን ትልቁን ነጻ የንግድ ቀጠናን ይፈጥራል ተብሎለታል።
የአፍሪካ ግዙፍ መጣኔ ሃብት ባለቤት ናይጄሪያ የነጻ ንግድ ቀጠና ስምምነት ላይ ፊርማዋን ማኖሯ የስምምነቱን ውጤታማነት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ኤርትራ ለምን ብቻዋን ቀረች?
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በነበራት አለመግባባት እና በሌሎች ምክንያቶች በስምምነቱ ዙሪያ ውይይቶች ላይ ተሳታፊ ሳትሆን መቆየቷን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ ይናገራሉ።
ኮሚሽነሩ ጨምረውም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም ማውረዷን ተከትሎ በስምምነቱ ዙሪያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ለመወያየት ጥያቄ ማቅረቧን ተናግረዋል።
''በጊዜ ሂደት እነሱም የስምምነቱ አካል ይሆናሉ'' ብለዋል ኮሚሽነሩ።












