ምርጫ 2013: 28 ሚሊዮን ተመዝግበዋል ለተባለው ምርጫ ምዝገባው ለተጨማሪ ቀናት ተራዘመ

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዲስ አበባ እና ድሬ ዳዋን ጨምሮ በክልሎች የመራጮች ምዝገባ ለተጨማሪ 7 ቀናት እንዲራዘም ማድረጉን አስታወቀ።

ቀደም ብሎ ይፋ በተደረገው ቀነ ገደብ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ከአፋር እና ከሶማሌ ክልል በስተቀር የሚጠናቀቀው ዛሬ ነበር።

ይሁን እንጂ ባለፉት ቀናት በተደራራቢ ብሔራዊ የበዓል ቀናት ምክንያት በርካታ የመራጮች መመዝገቢያ ጣቢያዎች ዝግ ሆነው መቆየታቸው እና ንኡስ ጣቢያዎችን ለማደራጀት ጊዜ መውሰዱን በመጥቀስ ምዝገባውን ማራዘም ማስፈለጉን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ቦርዱ ተቀዛቅዞ የነበረው የመራጮች ምዝገባ በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሎ በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት በተሰበሰበው መረጃ ከ28 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ መራጮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ብሎ ነበር።

በአሁኑ ወቅትም በ41,798 ምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ እየተከናወነ እንደሚገኝ ቦርዱ አስታውቋል።

ቦርዱ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር፣ በአማራ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል፣ በጋምቤላ ክልል፣ በሃረሪ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል እና በሲዳማ ክልል የመራጮች ምዝገባ እስከ አርብ ግንቦት 06 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ለተጨማሪ 7 ቀናት እንዲከናወን ወስኗል።

ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ በተከናወኑባቸው ስፍራዎች ነዋሪዎች በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ የቦርዱ አስፈጻሚዎች እና አስተባባሪዎች ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 06 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የመራጮች ምዝገባን እንዲያከናውኑ አስታውቋል።