ምርጫ 2013፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዝግጅት

16 ሳምንታት አካባቢ በቀሩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ፣ ምርጫውን በበላይነት የሚያስፈፅመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አንዳንድ ዝግቶቹን ማጠናቁን አስታውቋል።

የምርጫ ቦርዱ የምርጫው የጊዜ ሰሌዳን አስመልክቶ ባስቀመጠው መረጃ መሰረት ከታህሳስ 16-ጥር 16፣ 2013 ዓ.ም የምርጫ ክልል ቢሮዎችን መክፈት፣ እንዲሁም ከጥር 24- የካቲት 21 2013 ዓ.ም ለምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና ለመራጮች ምዝገባ የሚከናወን ይሆናል።

በዚህም የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የምርጫ ቢሮዎች ለመክፈት የሚያስፈልገው ትብብርን ማግኘት እንዳልቻለ ቅሬታውን አቅርቧል።

በአሁኑም ወቅት ለምርጫ ክልል እና ለዞን ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሊያገለግሉ የሚችሉ ቢሮዎችን አምስት ክልሎች ሙሉ በሙሉ ማሟላት አልተቻለም ብሏል። እነዚህም የተጠቀሱት ክልሎች አፋር፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፣ ሶማሌ ክልል ሲሆኑ እነዚህም ክልሎች የተጠየቁትን በሙሉ እስከ የካቲት 5፣ 2013 ዓ.ም ማጠናቀቅ አለባቸው ሲል አሳስቧል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ ጥር 10፣ 2013 ባወጣው መግለጫ ከክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች የሚያስፈልገው ትብብር ባለመሟላቱ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ለመክፈት ዝግጅት ማድረግ እንዳልቻለ ባስታወቀው መሰረት ከፍተኛ መሻሻሎች ታይተዋል ብሏል።

በዚህም መሰረት አዲስ አበባና ድሬዳዋ መስተዳድሮች፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ ሐረሪ ክልሎች ለምርጫ ክልልና ለዞን ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት የሚያስፈልጉትን ቢሮዎች በማዘጋጀት ለቦርዱ ማስታወቃቸው ተገልጿል።

በእነዚህ ቢሮዎችን ባሟሉ ቦታዎች የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው በሚያዘው መሰረት ከየካቲት 08-21፣ 2013 ዓ.ም የዕጩ ምዝገባ የሚካሄድ ሲሆን በቀሪዎቹ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ አሟልተው ሲያቀርቡ ምዝገባው እንደሚጀመር አስታውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 28፣ 2013 ዓ.ም ለሚደረገው ምርጫ የመራጮች ትምህርት ለማስተማር ዕውቅና ለተሰጣቸው የሲቪል ማህበራት ሰርቲፊኬትና ተያያዥ ሰነዶችን መስጠት መጀመሩን አስታውቋል።

ምርጫ ቦርዱ የመራጮች ትምህርት ለሚያስተምሩ ሲቪል ማህበራት ዕውቅና ለመስጠት ባወጣው ጥሪ መሰረት መስፈርቱን የሚያሟሉ ሲቪል ማህበራትን በመገምገም ጥር 13፣ 2013 ዓ.ም ለ24 ሲቪል ማህበራት ዕውቅና መስጠቱን አስታውሷል።

ቦርዱ ከዚህም በተጨማሪ በሁለተኛው ዙር እንዲሁ ለተጨማሪ 47 ሲቪል ማህበራት እውቅና መስጠቱን አስታውቆ፣ ማህበራቱ ለ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ትምህርት ለማስተማር የሚያስፈልገውን ሰርቲፊኬትና ተያያዥ ሰነዶች እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል።

ከምርጫ ዝግጅት ጋር በተያያዘ የምርጫ ቦርዱ ለምርጫ ክልል ኃላፊዎች ለምርጫ ጣቢያ ሰራተኞችና በተለያየ ደረጃ ላሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት ስልጠና መሰጠቱን እንዲሁ ገልጿል።

ስልጠናዎቹ ያካተቷቸው ርዕሶች የምርጫ የህግ ማዕቀፎች፣ የምርጫ ክልል ቢሮዎች ግዴታና ኃላፊነቶች፣ ለኮቪድ መከላከል ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎች፣ የምርጫ ቅሬታ አፈታቶች፣ የምርጫ ነክ ሎጂስቲክና ፀጥታ ሁኔታዎች ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ የስርዓተ ፆታና አካል ጉዳተኛ አካታችነት፣ የዕጩዎች ምዝገባ ሂደቶችን ጨምሮ ሌሎች ለምርጫው የሚያስፈልጉ አጀንዳዎች መካከል ናቸው።

ስልጠናው በቀጣይነት ለመሪ አሰልጣኞች የሚሰጥ መሆኑን አስታውሶ፣ እነዚህ መሪ አሰልጣኞች ደግሞ ወደተለያዩ ክልሎች በመሰማራት ምርጫ አስፈፃሚዎችን ያሰለጥናሉ ብሏል።

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ መራጮች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታወቆ ነበር።