ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ከፕሬዝደንት ኢሳያስ ጋር ተወያዩ
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ከኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተነጋገሩ።
በቅርቡ በፕሬዝደንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ፌልትማን፤ በቀጠናው ወደሚገኙ አገራት ጉዞ ማድረግ መጀመራቸው ይታወሳል።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሁለት ቀናት የሱዳን ጉብኝታቸውን አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ ከአምባሳደር ፌልትማን ጋር ረዘም ላለ ሰዓት መወያየታቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል አስታውቀዋል።
አራት ሰዓት በቆየው ውይይት ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ኤርትራ ከአሜሪካ ጋር አብራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል ሲሉ የማስታወቂያ ሚንስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው በበኩላቸው በአፍሪካ ቀንድ ስላሉ ችግሮች የአሜሪካ አስተዳደር መልዕከትን አብራርተዋል ብለዋል።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ቢሮ ልዩ መልዕከተኛው ከሚያዚያ 26 እስከ ግንቦት 5/2013 ዓ.ም ባሉት ቀናት ወደ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሱዳን ያቀናሉ ብሎ ነበር።
አምባሳደሩ የኤርትራውን ፕሬዝደንት ከማግኘታቸው በፊት ወደ ግብጽ አምርተው ከፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ፣ ከውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ሳሚህ ሽኩሪ እና ከአገሪቱ የውሃ ሚንስትር ጋር ስለመገናኘታቸው ተዘግቧል።
ፌልትማን በመጀመሪያው መዳረሻቸው ግብጽ ከፕሬዝደንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ ጋር ተገናኝተዋል። በውይይታቸው ወቅት አል-ሲሲ ግብጽ ከአባይ ውሃ የምታገኘው ድርሻ መቀነስን አትታገስም በማለት ስለመናገራቸው ዋሽግተን ፖስት ዘግቧል።
አምባሳደር ፌልትማን ከግብጽ ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ቆይታ የጆ ባይደን አስተዳደር በቀጠናው ላሉ አንገብጋቢ ጉዳዮች መፍትሄ ለመስጠት ትኩረት ያደርጋል ሰለማለታቸው ዋሽንግተን ፖስት ምንጮቹን ጠቅሶ ጨምሮ ዘግቧል።
ፌልትማን ማን ናቸው?
ጄፍሪ ፌልትማን በሹመታቸው ወቅት በተለይ በኢትዮጵያና በዙሪያዋ ስላሉ ሁኔታዎች የተለየ ትኩረት እንደሚሰጡ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ አስታውቆ ነበር።
ፌልትማን በድርድርና የሽምግልና ጉዳዮች ላይ ጥናትን በማካሄድና በአደራዳሪነትም ከፍ ያለ ልምድ እንዳላቸው ይነገራል።
ፌልትማን በፖለቲካዊና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞውንና የአሁኑን ዋና ጸሐፊዎች ባን ኪሙን እና አንቶኒዮ ጉቱሬዝን ያማከሩ ሲሆን፤ ለጸጥታው ምክር ቤት በሠላምና በደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያዎችን በመስጠት ይታወቃሉ።
በተባበሩት መንግሥታት ቆይታቸው ወቅትም በልዩ መልዕክተኝነት አገልግለዋል፤ በተጨማሪም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለ26 ዓመታት ያገለገሉት ፌልትማን በሊባኖስ፣ በኢራቅ፣ በእስራኤል፣ በቱኒዚያ፣ በሃንጋሪና በሄይቲ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል።
የሕዳሴ ግድብ
ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ላይ እየገነባች ያለችው ግዙፍ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ኃይል በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል ውጥረት ፈጥሯል። ሦስቱ አገራት በግደቡ ውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ዙሪያ ከስምምነት ለመድረስ ለበርካታ ዓመታት ሲያደርጉት የነበረው ድርድር እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አላስገኘም።
የቅርብ ጊዜያት ድርድሮችም ያለስምምነት መበተናቸው ይታወሳል።
ግብጽ እና ሱዳን የኢትዮጵያ ግድብ የውሃ ድርሻችንን ይቀንሳል ሲሉ ኢትዮጵያ በበኩሏ ከግድቡ የምታገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል በጭለማ ለሚኖሩ 60 ሚሊዮን ዜጎቼ ብርሃን ነው ትላለች።
ባሳለፍነው ዓመት ውሃ መያዝ የጀመረው ግድብ በዚህ ዓመት የክረምት ወራትም ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀድሞ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።