ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በቀጠናው ጉብኝት ማድረግ ጀመሩ
በቅርቡ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ አድርጎ የሾማቸው ጄፈሪ ፌልትማን በቀጠናው ወዳሉ አገራት ጉዞ ማድረግ መጀመራቸውን የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
ልዩ መልዕከተኛው ከሚያዚያ 26 እስከ ግንቦት 5 2013 ዓ.ም ባሉት ቀናት ወደ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሱዳን ያቀናሉ ተብሏል።
ልዩ መልዕክተኛው ጄፈሪ ፌልትማን በሚያደርጉት ጉዞ የየአገራቱን ባለስልጣናት ጨምሮ ከተባበሩት መንግሥት እና የአፍሪካ ሕብረት ተወካዮች ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ጄፈሪ ከፖለቲከኞች እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር እንደሚገናኙ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ቃል አቀባይ ቢሮ አስታውቋል።
የውጪ ጉዳይ ቢሮው በመግለጫው የልዩ መልዕክተኛው ጉዞ የጆ ባይደን አስተዳደር በአፍሪካ ቀንድ ያለው ፖለቲካ እና የደህንነት ችግር እንዲሁም የሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብሏል።
ፌልትማን ማን ናቸው?
ጄፍሪ ፌልትማን በሹመታቸው ወቅት በተለይ በኢትዮጵያና በዙሪያዋ ስላሉ ሁኔታዎች የተለየ ትኩረት እንደሚሰጡ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ አስታውቆ ነበር።
ፌልትማን በድርድርና የሽምግልና ጉዳዮች ላይ ጥናትን በማካሄድና በአደራዳሪነትም ከፍ ያለ ልምድ እንዳላቸው ይነገራል።
ፌልትማን በፖለቲካዊና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞውንና የአሁኑን ዋና ጸሐፊዎች ባን ኪሙን እና አንቶኒዮ ጉቱሬዝን ያማከሩ ሲሆን፤ ለጸጥታው ምክር ቤት በሠላምና በደኅንነት ጉዳዮች ማብራሪያዎችን በመስጠት ይታወቃሉ።
በተባበሩት መንግሥታት ቆይታቸው ወቅትም በልዩ መልዕክተኝነት አገልግለዋል፤ በተጨማሪም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለ26 ዓመታት ያገለገሉት ፌልትማን በሊባኖስ፣ በኢራቅ፣ በእስራኤል፣ በቱኒዚያ፣ በሃንጋሪና በሄይቲ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል።
ቀጣዩ ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ 'ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አያሟላም'
ጄፈሪ ፌልትማን ወደ ቀጠናው ጉዞ ከማድረጋቸው በፊት አምስት የአሜሪካ ሴናተሮች የተጻፈ ደብዳቤ ደርሷቸው ነበር።
ለልዩ መልዕክተኛው በጻፉት ደብዳቤ ኢትዮጵያ ከሳምንታት በኋላ ስለምታደርገው አገራዊ ምርጫ፣ ስለትግራይ እና በሌሎች የአገሪቱ ስፍራዎች ስላሉ ግጭቶች ለተሿሚው ልዩ መልዕክተኛ መልዕከታቸውን አጋርተዋል።
ሴናተሮቹ በደብዳቤያቸው አገራዊው ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ ነጻ፣ ሚዛናዊ እና ግልጽ ሆኖ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አያሟላም ብለዋል።