አምነስቲ፡ "የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የተቀዛቀዘ ምላሽ ለትግራይ ግጭት አስተዋፅዖ አድርጓል"

የአፍሪካና የተቀረው ዓለም መሪዎች በትግራይ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ድምፃቸውን የበለጠ እንዲያሰሙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ድርጅት ጥሪ አቀረበ።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተሟጋች ቡድን ባወጣው መግለጫ ለስድስት ወራት በዘለቀው የትግራይ ጦርነት በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተካሂደዋል ብሏል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ መቶ ሺዎች ክልል ውስጥ ተፈናቅለዋል፤ እንዲሁም 63 ሺህ ሰዎች ወደ ሱዳን ተሰድደዋል ብሏል ድርጅቱ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎች ተቋማት እስከ የጦር እና ሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀልን ጨምሮ የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅመዋል ይላል የድርጅቱ መግለጫ።

መግለጫው አክሎም የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች በጋራ መድፈርን ጨምሮ ታዳጊና አዋቂ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንደፈፀሙ ማስረጃዎች አሉ ይላል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በትግራዩ ግጭት ተፈጽመዋል የተባሉ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተመርምረው ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ የሠራዊቱ አባላት ለሕግ ይቀርባሉ ብለው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከአፍሪካ ሕብረት ሰብዓዊ አጥኒ ኮሚሽን ጋር የተፈጸሙ የመብት ጥሰተኞችን በጋራ እንደሚመረምሩ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

በሌላ በኩል ከመብት ጥሰቶቹ ጋር ተያይዞ ሰሙ በተደጋጋሚ ለሚነሳው የኤርትራ ጦር በተመለከተ አገሪቱ መንግሥት ከሶቹ መሠረተ ቢስ ናቸው ሲል አጣጥሎ ነበር።

"ስድስት ወራት ባስቆጠረው የትግራይ ግጭት የሰብዓዊ መብትና የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግጋት ጥሰቶች እንዳሉ የሚያሳዩ ማስረጃዎች እጥረት ባይኖርም ከአፍሪካ ሕብረትና ከተባበሩት መንግሥታት በቂ ምላሽ አልተሰጠም" ይላሉ የአምነስቲ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ኃላፊ ዴፕሮስ ሙቼና።

"የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ከወራት በኋላ በትግራይ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰበው ገልጿል። የአፍሪካ ሕብረትና የቀጣናው ሃገራት ግን በተነፃፃሪ ዝምታን መርጠዋል" ይላሉ ኃላፊው።

በሁሉም ወገን የተፈፀመ ጥሰት

የኢትዮጵያ መንግሥት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ወደ ትግራይ ለመግባት የጠየቀውን ፈቃድ ችላ በማለቱ አሁን ባለው አስቸጋሪ የግንኙነት መስመር ተፈፀሙ የተባሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ማጣራት ከባድ ነው ይላል የድርጅቱ መግለጫ።

ነገር ግን አምነስቲ፤ 'ኦፕን ሶርስ' የተሰኘ የምርመራ መንገድ እንዲሁም የሳተላይት ምስሎች ትንተና እና የቪድዮ ምስሎች ማስረጃዎችን በመጠቀም የተለያዩ ጥሰቶችን እንደመዘገበ በመግለጫው አሳውቋል።

አልፎም ድርጅቱ ከጥቃት የተረፉ ሰዎችን እንዲሁም በምስራቅ ሱዳን ያሉ ስደተኞችን በቴሌፎንና በአካል በማናገር መረጃ እንደሰበሰበ በመግለጫው አትቷል።

አምነስቲ መዝቤያቸዋለሁ ካላቸው ጥሰቶች መካከል በማይ ካድራ ከሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ ኃይሎች የተፈፀመው ጅምላ ግድያ እንደሚገኝበት አሳውቋል። ይህን ተከትሎ የትግራይ ተወላጅ በሆኑ የማይ ካድራ ነዋሪዎች ላይ የአፀፋ ጥቃት፣ ሕግን ከለላ ያደረገ ግድያ፣ ዘረፋና ጅምላ እሥር እንደተፈፀመ መመዝገቡን ይገልፃል።

አምነስቲ አክሎ በአክሱም ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውንና ይህም ሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችል እንዲሁም በአድዋ ከተማ ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በተፈፀመ ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን በመግለጫው አትቷል።

አምነስቲ ከሲኤንኤን ጋር ተባብሬ አረጋገጥኩት ባለው ወንጀል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በማሕበረ ደጎ ከተማ ሕግን ከለላ አድርገው በፈረንጆቹ ጥር 15/2021 ግድያ ፈፅመዋል ብሏል በመግለጫው።

ወደ ትግራይ እንዲገቡ በየካቲት ወር ፈቃድ የተሰጣቸው መገናኛ ብዙሃን በአምነስቲና ሌሎች ድርጅቶች ተፈፅመዋል ተብለው የተጠቀሱትን ጥሰቶች እንዳረጋገጡና አስከፊ ጥሰቶችን እንዳጋለጡ ድርጅቱ ይገልፃል።

በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ወኪሎችና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በለቀቁት መግለጫ "እየጨመረ የመጣው በሕፃናትና አዋቂ ሴቶች ላይ የሚፈፀም ወሲባዊ ጥቃት" እንዳሳሰባቸው "ለዚህ ጥቃት የተሰጠው ምላሽ በቂ እንዳልሆነ" ገልፀዋል ይላል አምነስቲ።

በሌላ በኩል የሰብዓዊ እርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ሆስፒታሎችና ሌሎች የጤና ተቋማት ጥቃት እንደደረሰባቸውና እንደተዘረፉ ዘግበዋል ይላል የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ።

"ዓለም እየተመለከተ በትግራይ ያሉ አዋቂና ታዳጊ ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት እየተጋረጠባቸው መሆኑ ትክክል አይደለም። ሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎችና ሆስፒታሎች አቅርቦታቸው በግጭቱ ምክንያት በመጎዳቱ የእርዳታ አቅም የላቸውም" ይላሉ ዴፕሮስ ሙቼና።

የሰብዓዊ እርዳታ ክልከላና የረሃብ ስጋት

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በተደጋጋሚ በትግራይ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ አካላት ለእርዳታ ሰጪዎች መንገድ እንዲሰጡ መጠየቁን በመግለጫው ያትታል።

በፈረንጆቹ ከሚያዚያ 27/2021 ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት መሻሻል እንዳለ ቢገልፅም "በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ አሁንም የተረጋጋ አለመሆኑና እርዳታ በጊዜው እንዲደርስ እንዳላስቻለ" ገልጿል ይላል አምነስቲ።

በወርሃ መጋቢት ብቻ ድንበር አልባው የዶክተሮች ቡድን [ኤምኤስኤፍ] በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ የነበራቸው ተልዕኮ ሁለት ጊዜ መቋረጡን አምነስቲ ይናገራል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የሰብዓዊ እርዳታ እያቀረበ መሆኑን እና ለበርካቶች ተደራሽ ለመሆኑን ከተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

በመጀመሪያው አጋጣሚ ድንበር አልባው የዶክተሮች ቡድን ወታደሮች ሕግን ከለላ ያደረገ ግድያ ሲፈፀም ማየቱን፣ እንዲሁም ወታደሮች የቡድኑን መኪና አስቁመው ኢትዮጵያዊውን አሽከርካሪ እንደደበደቡና የግድያ ዛቻ እንዳደረሰቡት የአምነስቲ መግለጫ ያወሳል።

በትግራይ በግብርና ምርት የሚተዳደሩ ቦታዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው እንዲሁም ሰብል ሆን ተብሎ እንዲወድም በመደረጉ የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች ድርጅቶች አስከፊ የምግብ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ከማስጠንቀቁም በላይ ጉዳዩ ወደ ረሃብ የማምራት ስጋት እንዳለው አምነስቲ ፅፏል።

አምነስቲ መግለጫውን ሲያገባድ እንደ አማራ፣ ቤኒንሻንጉል እንደ ኦሮሚያ ክልል ባሉ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ነው ብሏል።

በጭልጋ ወረዳ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በአማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ በቤኒንሻንጉል ክልል በመተከል ዞን ንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈፀሙ እንደተዘገበ፤ እንዲሁም በምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች የታጠቁ ሰዎች የአማራ ተወላጆችን እንደገደሉ እንዳፈናቀሉ አምነስቲ ጠቅሷል።

"ዓለም አቀፍና ገለልተኛ መርማሪዎች በሁሉም ወገኖች ተፈፅመዋል የተባሉትን ጥሰቶች ማጣራት አለባቸው። ጥፋቱን ፈፅመው የተገኙ ሊጠየቁ ይገባል። ከፍርድ የሚድን እንደሌለ መልዕክት መላክ ያሻል" ይላሉ ሙቼና።

"ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በትግራይ ክልል ስላለው ግጭት ያለው ምላሽ የተቀዛቀዘ ከሆነ አሁን ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል።"

የአምነስቲን ሪፖርት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት አስተያየት በዚህ ዘገባ ላይ ለማካተት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።