ትግራይ፡ በኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት ጎረቤት አገራትን ያሰጋ ይሆን?

በኢትዮጵያ በፌደራል መንግሥቱና እና በትግራይ ክልል መስተዳደር መካከል የሚደረገው ውጊያ በአገሪቱ መጻዒ ዕጣ ላይ ከሚደቅነው ፈተና በተጨማሪ የጎረቤት አገራትንም በእጅጉ ይጎዳል።

ጦርነቱ በተጀመረ በቀናት ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "የኢትዮጵያ የተረጋጋች አገር መሆን ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና በአጠቃላይ አስፈላጊ ነው" ብለው ነበር።

ኢትዮጵያ ከ110 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት ሲሆን ምጣኔ ሃብቷም በአህጉሪቱ ካሉ ሌሎች አገራት ጋር ሲነጻፀር በፍጥት እያደገ መሆኑ ጦርነቱ በአገሪቱ ላይም ተጽዕኖው ቀላል እንዳይሆን ያደርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መንግሥት ከትግራይ ክልል ጋር ያለውን ልዩነት በድርድር እንዲፈቱ ከተለያዩ የዓለም መንግሥታት የቀረበላቸውን ጥሪ "የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይከበሩ" በሚል ችላ ብሏቸዋል።

መንግሥት ግጭቱን በኢትዮጵያ ያለውን የሕገ መንግሥት ሥርዓት ለማፍረስ ከሚጥር አካል ጋር የሚደረግ "የሕግ ማስከበር" ተግባር መሆኑን ይገልጻል።

ይህ ጦርነት በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል ለረዥም ጊዜ የነበረን ውጥረት ተከትሎ የመጣ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች የአየር ድብደባውን እና ውጊያውን ሽሽት ወደ ጎረቤት ሱዳን ሸሽተዋል።

"ተጽዕኖው ከፍተኛ ነው"

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ራሺድ አብዲ "ጦርነቱ ቀጠናዊ ነው" ሲሉ ይሞግታሉ።

"ሱዳናውያን ተሳተፈዋል እንዲሁም ሌሎች አገራትም አንድ ቦታ ላይ መሳተፋቸው አይቀርም፤ ምክንያቱም ስትራቴጂካዊ አገር [ኢትዮጵያ] ናት። ስለዚህ ተጽዕኖው ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

እንደ ራሺድ ከሆነ ከትግራይ ክልል ጋር ረዥሙን ድንበር የምትጋራው ኤርትራም ወደ ጦርነቱ መጎተቷ አይቀርም።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ደግሞ የትግራይን ክልል ከሚያስተዳድረው ፓርቲ ህወሓት ጋር ያላቸው ግንኙነት የሻከረ ነው። በተቃራኒው ፕሬዝዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር ደግሞ የቅርብ አጋር ናቸው።

እስካሁን ግን የኤርትራ መንግሥት በፌደራል እና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል ባለው ጦርነት ውስጥ እጁ እንደሌለበት ገልጿል።

በሌላ ወገን የፌደራል መንግሥቱ ትኩረቱን ሁሉ በትግራይ ክልል ላይ ማድረጉ በሶማሊያ የአልሸባብ አማፂያንን ለመከላከል የሚያደርገው ተሳትፎን እንደሚያዳክመው ራሺድ አብዲ ይገልጻሉ።

አክለውም ኢትዮጵያ ምንም እንኳ የአፍሪካ ሕብረት ያሰማራቸው የአሚሶም ጦር አባላት ባይሆኑም፣ ከሶማሊያ ምዕራባዊ ድንበር 600 ወታደሮቿን አስወጠታለች። "ሁኔታዎች ከዚህ በላይ እየከፉ የሚሄዱ ከሆነ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከአሚሶምም ሊወጡ ይችላሉ፣ ያ ደግሞ ከባድ ቀውስ ነው. . . አልሸባብ ዳግም እንዲጠናከርና እንዲሰባሰብ ያደርገዋል" ይላሉ።

ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕም ግጭቱ በፍጥነት ካልቆመ "ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድን በአጠቃላይ ቀውስ ውስጥ ይጥላል" በማለት በዚህ ሃሳብ ይስማማል።

ኢትዮጵያስ እንደ አገር?

የሁለቱ መንግሥታት ጦርነት የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ እንዳለ ሆኖ ጦርነቱ ኢትዮጵያንም እንደ አገር ያዳክማታል የሚሉ ወገኖች አሉ።

ያ ደግሞ ኢትዮጵያ በቀጠናው ላይ ባላት ተሳትፎ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ሌሎች በአገሪቱ የሚገኙና ነፍጥ አንስተው ለመታገል የወሰኑ ወገኖች በማዕከላዊ መንግሥቱ ላይ እንዲያምፁ ያደርጋቸዋል።

አብዲ ረሺድ ይህንን ሲያስረዱ "እያየነው ያለነው ምንድን ነው ተጽዕኖው ከማዕከል እየራቀ ማዕከላዊው መንግሥት ደግሞ እየተዳከመ መሆኑን ነው" ይላሉ።

ይሀ ግን መቀመጫውን ናይሮቢ ላደረገው የአፍሪካ ቀንድ ቲንክ ታንክ ተቋም ባልደረባ ሃሰን ካህናንጄ አልተዋጠለትም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሁን እየወሰዱት ያለው እርምጃ የትግራይ ክልል መንግሥትን ወደ ሕጋዊ መስመር ለማምጣትና ሌሎችም እንደ ምሳሌ ወስደው እንዳይከተሉት የማድረግ ነው ሲል ይሞግታል።

"ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ይህንን የሚያየው ለሌሎች ክልሎች መጥፎ ምሳሌ እንደሆነ ነው. . . ወደ መገንጠል የሚያመራ የተናጠል ውሳኔ ለኢትዮጵያ መነጣጠል ነው፤ ያ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠሏ ያበቃል ማለት ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግሯል።

"የመጨረሻው ግብ ክልሉን ወደ ፌደራላዊ ሥርዓቱ በማምጣት እንደ አንድ አገር ምርጫ ማካሄድ ነው። በተግባር ሲታሰብ በጣም ከባድ ቢሆንም የማይቻል ግን አይደለም።"

በዚህ መካከል ቀውሱን በመፍራትም ሆነ በመሸሽ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቤታቸውንና ቀያቸው ጥለው ይሰደዳሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ቃል አቀባይ አርብ ዕለት ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት፣ በአካባቢው እየመጡ ያሉ የስደተኞች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን "አሁን እርዳታ ማቅረብ ከምንችለው በላይ ነው" ብለዋል።

የሱዳን መንግሥትም 20ሺህ ሰዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችል የስደተኞች መጠለያ ከድንበሩ በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለመገንባት ፈቃደኛ መሆኑ እና ሌሎች አካባቢዎችም መለየታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

አካባቢው በበረሃ አንበጣ የተጎዳ መሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ የምግብ እጥረት እንዲከሰት ማድረጉን የጠቀሰው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ሌላ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ዳግም ሊከሰት እንደሚችል ተንብይዋል።

ትግራይ ክልል ከአጠቃላይ ሕዝቡ 10 በመቶ ያህሉ፣ 600ሺህ ያህሉ የምግብ እህል እርዳታ የሚጠብቅ ሲሆን፣ በመላ አገሪቱ ደግሞም ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ለምግብ እጥረት ተጋላጭ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይገልጻል።

ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት ይጨምራል።

ኢትዮጵያ ያላት ከፍተኛ ሕዝብ ቁጥርና ስትራቴጂካዊ ስፍራነቷ በኢትዮጵያ የሚከሰት ጦርነትም፣ የሰብዓዊ ቀውስ ሆነ ማንኛውንም ነገር ወደ ሌሎች አይዛመትም ብሎ መደምደም አይቻልም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ግን ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለመቋጨትና ጉዳዩ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ነው በሚል አቋማቸው እንደፀኑ ናቸው። ነገር ግን ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ባይሳካና ለረዥም ጊዜ አገሪቱ ጦርነት ውስጥ የምትቆይ ከሆነ ጦሱ ለጎረቤት አገራትም መትረፉ አይቀሬ ነው።