ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለምን መከላከያውን ወደ ትግራይ አዘመቱ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፋቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ላይ ጦርነት ምን ያክል አስከፊ እንደሆነና ምን ያክል እንደሚያጨካክን በስሜት ተናግረው ነበር።
ላለፉት ሦስት ሳምንታት የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የህወሓት አመራሮችን በሕገ ወጥነት በመፈረጅ ጦርነት ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚንስት ዐብይ ተመርጠው ብዙም ሳይቆዩ መገናኛ ብዙሃንን በሰበር ዜና ያጥለቀለቁ ውሳኔዎች ማስተላለፋቸው ይታወሳል
ሞት ተፈርዶባቸው የነበሩ እሰረኞች ነጻ ወጡ፣ አሸባሪ ተብለው በነበሩ አካላት ምትክ መንግሥት "አሸባሪዎቹስ እኛ ነን" በማለት ብዙዎችን ከእስር ለቀቀ። ከኤርትራ ጋር እርቀ ሰላም የማውረድ ጅማሮ ታየ።
ወቅታዊ ዜናዎችን ያደመጡ ኢትዮጵያን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ጋዜጠኞችም "እንዲህ ከሆነማ ወደአገራችን እንመለሰላን" ብለው ሻንጣቸውን አነሱ።
መንግሥት አላስነካ ብሏቸው የነበሩት የኃይል፣ ቴሌኮሚዩኒኬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ መንግሥታዊ ተቋማትን ለአገር ውስጥና ለውጪ ባለሀብቶች ድርሻ እሰጣለሁ አለ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ ጥቅምት 24/2013 ዓ. ም የትግራይ ኃይሎች በትግራይ የሚገኘው ትልቁንና በትጥቅ የተደራጀው የመከላከያ ሠሜን ዕዝ ካምፕ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልፀው ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።
ውጥረቱ ወደ ወታደራዊ ግጭት ከማምራቱ በፊት በፌደራል መንግሥትና የትግራይን ክልልን ይመራ በነበረው ህወሓት መካከል የቆየው መቃቃር የተባባሰው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ፓርላማው በአገሪቱ ታቅዶ የነበረው ምርጫ እንዲራዘም የሰጡትን ውሳኔ ባለመቀበል የትግራይ ክልል የተናጠል ምርጫ ማድረጉን ተከትሎ ነው።
የእስር ማዘዣ
በሌላ በኩል በኬል ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የሕግ መምህር የሆኑት አወል አሎ (ዶ/ር)፤ 'ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም አገሪቱን ለመበታተን በመስራት' በሚል በፌደራል ፖሊስ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸዋል።
የፌደራል ፖሊስ አወልን (ዶ/ር) ጨምሮ የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም አገር አፍራሽ መረጃ ያሰራጫሉ ባላቸው ሰባት ግለሰቦች እና በ27 ወታደራዊ ሹማምንት ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ማውጣቱን ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
''በዚህ ሰዓት በቁጥጥር ስር እንድውል ማዘዣ ስለመውጣቱ አላውቅም፤ ነገር ግን ወደ ኢትዮጵያ መሄድ ከፍተኛ ስጋት እንደሚፈጥር አውቃለው'' ብለዋል አወል (ዶ/ር) ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ።
''ተቃዋሚዎችን ዝም ከማሰኘት አንጻር በቀድሞው መንግሥትና በአሁኑ መካካል ምንም ልዩነት የለም። የሕግ ሥርዓቱን ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል፣ ተቃዋሚዎችንና የተለየ አመለካከት ያላቸውን ጸጥ ለማድረግ ነው እየተጠቀሙበት ያሉት።''
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ ጦርነቱ በተወሰኑ የህወሓት አባላት ላይ ያነጣጠረ ሕገ መንግሥትን ለማስከበር እየተወሰደ ያለ እርምጃ መሆኑን ገልፀው በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ መግለፃቸው ይታወሳል።
የትግራይ ክልል በበኩሉ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጦርነት እንደተከፈተበትና ሕዝቡ ላይ ያነጣጠረ ነው ይላል።
መቀመጫውን ጄኔቫ ያደረገው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊው ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖምም ቢሆኑ ስማቸው ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ተነስቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስን በተመለከተ ቅሬታ እንዳለውና ደስተኛ አለመሆኑን አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
በተጨማሪም ዶ/ር ቴድሮስ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኘው ህወሓትን የሚደግፍ የማግባባት ሥራ አከናውነዋል ሲሉ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ከሰዋል።
ዶክተር ቴድሮስ አድሐኖም በበኩላቸው በኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት በኩል ከመንግሥት ሠራዊት ጋር ግጭት ውስጥ የገባውን ህወሓትን ለመደገፍ ጥረት አድርገዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ አድርገዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ ለቀረበባቸው ክስ በትዊተር ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ባለው ነገር ልባቸው እንደተሰበረ ገልጸው "በዚህ ውስጥ አንድ ወገንን እንደደገፍኩ የሚገልጹ ዘገባዎች ሲወጡ ቆይተዋል። ነገር ግን ይህ እውነት አይደለም" ብለዋል።
ጨምረውም "እኔ የምደግፈው አንድ ወገን ቢኖር ሠላም የሚመጣበትን መንገድ ብቻ ነው" ሲሉ ለሠላም ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ምንይችል መሰረት በበኩላቸው፤ ኢላማ የተደረጉት ሰዎች በሙሉ ከሕወሓት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ናቸው በማለት የመንግሥትን እርምጃ ደግፈዋል።
''ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከዚህ በፊት ተዘግተው የነበሩ 264 ድረ ገጾች ተከፍተዋል። አሁን እየሆነ ያለው አጠቃላይ የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ የሚገልጽ አይደለም። አገሪቱ ትልቅ አደጋ ላይ ነበረች። ህወሓት በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል የሚገኝ ወታደራዊ ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽሟል። የትኛውም አገር ይህንን አይታገስም'' ብለዋል።
አወል (ዶ/ር) ግን ''ዋናው ጥያቄ የመጀመሪያውን ጥይት ማን ተኮሰ አልያም ማነው ጥፋተኛው የሚለው አይደለም፤ ዋናው ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መቀመጫውን አዲስ አበባ ካደረገው የአፍሪካ ሕብረት እንኳን የቀረበላቸውን የድርድር ሀሳብ ውድቅ ማድረጋቸው ነው'' ይላሉ።
''እንደ አንድ መንግሥት የሚያስፈልገው ትዕግስት፣ መቻቻልና ለሰላምና እርቅ ቅድሚያ መስጥት ነው። የሚያሳዝነው ግን ሁለቱም ወገኖች ለጦርነት ሲዘጋጁ ነበሩ።''
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በነሐሴ ወር ሊካሄድ ታስቦ የነበረው አገር አቀፍ ምርጫ እንዲራዘም መደረጉን ተከትሎ ህወሓት፤ የ2012 አገራዊ ምርጫ በማንኛውም ሁኔታ መካሄድ አለበት፤ ምርጫ የማይካሄድ ከሆነ በክልል ደረጃ ምርጫ እናካሂዳለን የሚል አቋም አንጸባርቆ ነበር።
በወቅቱ የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ስድስተኛው ዙር ምርጫን እንዲያስፈጽምለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።
ምንም እንኳ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትግራይ ክልል ለማካሄድ የጠየቀውን የክልላዊ ምርጫ ለማስፈጸም የሚያስችለው ሁኔታ የለም ቢልም፤ የትግራይ ክልል የሚያቋቁመው አካል ምርጫውን እንደሚያስፈጽም የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ለቢቢሲ አስታውቀው ነበር።
በትግራይ ክልል ጳጉሜ 4/2012 ዓ. ም በተደረገው ክልላዊ ምርጫም ህወሓት በበላይነት ማሸነፉ እንደተገለጸ ይታወሳል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይና በህወሓት አመራሮች መካከል ከፍተኛ መቃቃር የተጀመረውም በዚህ ወቅት እንደሆነ አወል (ዶ/ር) ያስታውሳሉ።
''ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህወሓት አመራሮች እውቅና አይሰጡም፤ የሕወሓት አመራሮችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ ወጥ ናቸው በማለት እንደማይቀበሉ ገልጸው ነበር። ለጦርነቱ መቀስቀስ ይሄ ትልቅ ምክንያት ነው።''
በሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት ተከትሎም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የአገር መከላከያ ሠራዊት በህወሓት ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ መሰጠቱን በወቅቱ ይፋ አድረገዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው "ይህንን ጡት ነካሽ ኃይል ለማሳፈር እና ለመደምሰስ አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን እገልጻለሁ" ብለው ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትሩ መከላከያ ሠራዊት አገር የማዳን ግዳጅ እንደተሰጠውም አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ "ህወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል" ብለዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ "ብዙ ጊዜ የሠላም ስምምነቶች እንደተፈረሙ የሚጣሱ በመሆናቸው ጥፋተኞችን ለፍርድ ከማቅረብ ይልቅ የኃይል ድርጊትን የሚያበረታታ ነው" በማለት የውጭ ሽምግልና አስፈላጊነትን ጥያቄ ውስጥ ከተውታል።
ለውጡና ፌደራሊዝም
"በአገሪቱ ፍትሕ የለም" የሚሉት ዶ/ር አወል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ባለፈው ሐምሌ ወር ብቻ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በእስር ቤት ይገኛሉ ይላሉ።
''ምናልባት በትግራይ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ደግሞ የሚታሰሩ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ሊጨምር ይችላል'' ሲሉ ያስረዳሉ።
ተመሳሳይ አስተያየት የሚሰጡት በአሜሪካው ፒስ ኢንስቲቲዩት ውስጥ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ፓይተን ኖፍም "የፖለቲካው መድረክ በድጋሚ ተዘግቷል። ታዋቂ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ታስረዋል፤ ለዐብይ ወደ ስልጣን መምጣት ጉልህ ሚና የነበራቸው ለማ መገርሳ በቤታቸው ውስጥ በቁም እስር ላይ ናቸው" ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ምንይችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በፊት የነበረውን "ጨቋኝ'' ሥርዓት አስወግደዋል ብለው ይከራከራሉ።
''ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታግደው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲመለሱ አድርገዋል። የማረሚያ ቤት ሥርዓቱ እንዲሻሻል አድርገዋል። በርካቶች ከስደት ወደ አገራቸው እንዲገቡ አድርገዋል። ችግሩ የተፈጠረው በብሔር ፖለቲካ የሚጠቀሙ ፖለቲከኞች እዚም እዚያም ግጭት እንዲቀሰቀስ በማድረጋቸው ነው'' ይላሉ።
አቶ ምንይችል አክለውም ህወሓት ከአውሮፓውያኑ 1991 ጀምሮ ክልሎችን በፌደራላዊ ሥርዓት ስም በብሔር በመከፋፈል አገሪቱን ለዚህ ችግር እንደዳረጋት ይገልጻሉ።
''የብሔር ፌደራሊዝም ለአገሪቱ መከራን ነው ያሸከማት። አንዳንድ ብሔሮች የሆነ አካካባቢ የእነሱ ብቻ እንደሆነና ሌሎች ሰዎች መኖር እንደማይችሉበት እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። በዚህ ፌደራሊዝም ምክንያት ሰዎች ከመኖሪያቸው ተባርረዋል፤ ተገድለዋል፤ ተቃጥለዋል'' ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚተቹ ሰዎች እንደሚሉት፤ አሁን ያለው ብሔርን መሰረት ያደረገ ፌደራላዊ ሥርዓት የሚወገድ ከሆነ በአጼ ሚኒሊክና በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ወደነበረው ንጉሣዊ ሥርዓት ይመለሳል።
ይህም ሌሎች ማኅበረሰቦች በግድ ተጨፍልቀው የአማራውን ባህል እንዲቀበሉ የሚያደርግ ነው ብለው ቢከሱም፤ በርካቶች ይህ ሐሰት ነው ሲሉ ያስተባብላሉ።
"የጠቅላይ ሚኒስትሩ ራዕይ ቀደም ሲል የነበረውን የኢትዮጵያ ባሕላዊ የሥልጣን መዋቅርን የሚመስል ነው" የሚሉት ከአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ተቋም የሆኑት ፋይሰል ሮብሌ "ይህም በአማራ ባህል ዙሪያ የሚያጠነጥንና ልክ እንደራሳቸው ከዚሁ ጋር መመሳሰልን የሚቀበል ሥርዓት ነው" ይላል።
ለዚህም ምሳሌ ሲያስቀምጥ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምኒልክን ያወድሳሉ። ቤተ መንግሥታቸውንም መልሰው ገንብተውታል። ኢትዮጵያን መልሰው ታላቅ ለማድረግ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ። ነገር ግን የሚያልሟት ኢትዮጵያ ብሔሮች ችላ የተባሉባት ናት። የሚያደንቋቸውን ንጉሥ ሌሎች ወራሪና በባርነት የፈነገሏቸው እንደሆኑ ነው የሚያስቧቸው" ሲል ፋይሰል ይናገራል።
አዲስ አቅጣጫ
ፈይሰል ባለፈው ዓመት ኢህአዴግን ተክቶ የተመሰረተውን አዲሱን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፓርቲ በተመለከተም ሲናገር፤ ቀደም ሲል ኢህአዴግ ከ10ሩ የአገሪቱ ክልሎች የሚያስተዳድረው አራቱን ነበር።
አዲሱ ብልጽግና ፓርቲ ሲፈጠር የፓርቲው የተጽዕኖ ክልል ሰፍቶ ከትግራይ ክልል ውጪ ሁሉንም ክልሎች ማቀፍ ቻለ "በዚህ ጦርነትም ትግራይን ለመቆጣጠር ችሏል" ሲል ፈይሰል ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን እንደመጡ ሕዝቡ "የጠበቀው የፖለቲካ ብዝሃነት፣ በአገሪቱ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች ሰፋ ያለ የባህልና የቋንቋ እውቅና ማግኘት ነበር። ነገር ግን አሃዳዊ ሥርዓትን መርጠዋል" ብሏል።
ምንይችል ግን ከፈይሰል በተለየ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፖለቲካዊ ብዝሃነትና ለየትኛውም ብሔር ስጋት አይደሉም ይላል።
"አንድነት ማለት ለብዙ ሺህ ዘመናት የያዝከውን የብሔር ማንነት ደብቅ ወይም አጥፋው ማለት አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያሉት ያለው 'እያንዳንዱ ፖለቲከኛ ስለእራሱ ብሔር ከሚያስበው በመውጣት ወደ ፊት እንደሂድ። ግድያዎችን እናስቁም። በአንድነት በወንድማማችነትና በእህትማማችነት ስለምንኖርባት ኢትዮጵያ እናስብ' ነው።"
"ብልጽግና ይህንኑ እያደረገ ነው ያለው። በኢህአዴግ ወደጎን ተገፍተው የነበሩትን ሶማሊዎችን የመሰሉ ማህበረሰቦች ወደ አንድነት አምጥተዋል" ሲል ምንይችል ገልጿል።
በከፍተኛ ደረጃ ጽንፍ የወጡ አመለካከቶች ባሉባት ኢትዮጵያ "መንግሥት ፖለቲካዊ ቁርሾዎችንና ቅሬታዎችን የሚያስተነፍስበት መንገድ ማመቻቸት አለበት" የሚሉት ኖፍ ናቸው።
"አገሪቱን ወደ አዲስ አቅጣጫ የሚወስድ አማራጭ የለም። ከዚያ ይልቅ በተደራጀ መልኩ ውይይቶች ያስፈልጋሉ፤ ነገር ግን የፖለቲካ መሪዎች እስር ቤት ሆነው ይህንን ማድረግ አይቻልም" ሲሉም ኖፍ ያክላሉ።
በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት ዶ/ር አወልም "ሽግግሮች በአንድ ፓርቲ የሚመሩ ሳይሆኑ ሁሉን አቀፍ መሆን አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣኑን በማዕከል ይዘውታል። ሁሉም ነገር እሳቸው እንዲመነጭ ይፈልጋሉ" ይላሉ።
የኖቤል ሽልማት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ያለፈው ዓመት የሠላም የኖቤል ሽልማትን ያገኙት በቀዳሚነት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለሁለት አስርታት የቆየውን የድንበር ፍጥጫ እንዲያበቃ በማስቻላቸው ቢሆንም በተጨማሪም በአገራቸው ውስጥ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ እርምጃ በመውሰዳቸው ነው።
ሽልማቱ በጥድፊያ የተሰጠ ነው የሚሉት ኖፍ "የድንበር መተላላፊያዎች ለአጭር ጊዜ ተከፍተው ተዘጉ። ስለ ሰላም ስምምነቱ በጽሁፍ የሰፈረ ነገር የለም። በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል የተደረሰ መግባባት ነው። በዚህ መልኩ አይደለም ሰላም ማስፈን የሚቻላው" ይላሉ።
በአሜሪካ የሚገኙት ሌላኛው ተንታኝ አሌክስ ደ ዋል በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ህወሓትን ለማሸነፍ የተደረገ "የደኅንንት ስምምነት" ነው የሚመስለው ይላሉ።
"ኤርትራ በጦርነቱ ከፍ ያለ ሚና ነበራት። በትግራይ ውስጥ 20 ያህል ብርጌዶች እንደነበሩ የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ወጥተዋል። የኢትዮጵያ ወታደሮችም ወደ ኤርትራ ገብተው ነበር" ቢሉም ሁለቱም አገራት ይህንን ሐሰት ሲሉ ያስተባብላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለኖቤል ሽልማት ካጩት ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር አወል፤ "አሁን የሆነውን ባውቅ ኖሮ አላደርገውም ነበር። የኖቤል ሽልማት ማግኘት ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ጦርነት ውስጥ የሚገባ ከሆነ ደግሞ ኃላፊነትን ያስከትላል" በማለት ባለሁለት መልክ መሆኑን ይገልጻሉ።