በተለያዩ የአማራ ከተሞች ግድያና ጥቃቶችን በመቃወም ሰልፎች ተካሄዱ

በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች በንሑሃን ዜጎችን ላይ የሚፈጸሙ ግድያና ጥቃቶችን በመቃወም ሰልፎች ተካሄዱ።

የተቃውሞ ስልፍ ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከል የክልሉ መዲና ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወልዲያ፣ ደሴ፣ ሐይቅ እና ሰቆጣ ከተሞች ይገኙበታል።

ትናንት የተቃውሞ ሰልፍ ያካሄዱት ደሴ እና ደብረ ማርቆስ ከተሞችም በተመሳሳይ ዛሬም ለሁለተኛ ቀን አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ በዋናነት በንሑሃን ዜጎች ላይ የሚደርሱትን ግድያ እና ጥቃቶች የሚያወግዙ ድምጾች ተሰምተዋል።

ሰልፈኞች በቅርቡ በሰሜን ሸዋ የንሑሃን ዜጎችን ሕይወት መታደግ ባለመቻሉ ክልሉን እያስተዳደረ የሚገኘውን ብልጽግና ፓርቲ እና መንግሥትን አውግዘዋል።

የክልሉ መገናኛ ብዙሃን በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች፤ ተቃዋሚዎች በአማራ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግድያና መፈናቀል አውግዘዋል ሲል ዘግቧል።

በተመሳሳይ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በባሕር ዳር፣ በደብረ ማርቆስ እና ወልደያ ከተሞች በአማራ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ማንነትን መሠረት ያደረገ ግድያ የሚያወግዙ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል ብሏል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙን ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ ዞኖች እና በቤኒሻንጉል ክልል ማንነትን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች የበርካቶች ሕይወት አልፏል።

በተለይ ማክሰኞ ዕለት ለተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ምክንያት የሆነው በሰሜን ሸዋ ዞን የተፈጸመው ጥቃት ሲሆን አስካሁን በዚህ ሳቢያ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ በውል ባይታወቅም ሮይተርስ የዜና ወኪል ነዋሪዎችን ተቅሶ እንደዘገበው ቢያንስ 50 ሰዎች ሞተዋል ብሏል።

ቢቢሲ ያናገራቸው የአካባቢው አስተዳዳሪ እንደተናገሩት በዞኑ ውስጥ ባሉ ከተሞች ከባድ ንብረት ማውደም መፈጸሙንና በተለይ አጣዬ ከተማ በጥቃቱ ክፉኛ መጠቃቷን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት የሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞኖች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ጥቃቶችና ባጋጠሙ ግችቶች በሰውና በንብረት ላይ ተደጋጋሚ ጉዳት ደርሷል።

ባለፈው መጋቢት ወር ባጋጠመ ተመሳሳይ ሁኔታ ከ300 መቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ተቋም ኃላፊ የሆኑትን አቶ እንዳለ ኃይሌን ጠቅሶ ዘግቧል።