የቴስላ የገበያ ደርሻ መዳከሙን ተከትሎ ኤለን መስክ ቁጥር አንድ ባለጠጋ መሆኑ ቀረ

ኤለን መስክ የሐብቱ ዋና ምንጭ የሆነው የቴስላ የኤሌክትሪክ መኪና አክሲዮን ዋጋ በመቀነሱ በዓለም የሐብታሞች ደረጃ የቀዳሚነቱን ቦታ አጥቷል።

በጥር ወር መጀመሪያ ላይ ከ 880 ዶላር በላይ የደረሰው የቴስላ አክሲዮኖች ዋጋ አሁን ላይ 20 በመቶ በላይ አሽቆልቁሏል።

ኩባንያው በቅርቡ በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ቢትኮይን ላይ ኢንቨስት በማድረጉ ምከንያት የቴስላ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።

ይህን ተከትሎም የአማዞኑ አለቃ ጄፍ ቤዞስን በሐብታሞች ዝርዝር ውስጥ ወደ ነበረበት ቀዳሚ ቦታ ተመልሷል።

ምንም እንኳን ኩባንያው የገበያ ደርሻው መቀነሱ ችግር ውስጥ ባይከተውም፤ ኩባንያው ከቢትኮይን ጋር መያያዙ አንዳንድ የቴስላ ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ድርሻቸውን እንዲሸጡ አነሳስቷቸዋል ሲሉ የዌድቡሽ ሴኩሪቲሱ ተንታኝ ዳን ኢቭስ ተናግረዋል።

ቴስላ በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ቢትኮይን መግዛቱ እና ቢትኮይንን እንደ ክፍያም ለመቀበል ማቀዱን ተከትሎ የቢትኮይን ዋጋ በቅርብ ሳምንታት በ50 በመቶ አድጓል።

እንደ ማስተርካርድ እና የኒው ዮርክ ባንክ ያሉ ዋና ዋና ኩባንያዎች ቴስላን ተከትለው የዲጂታል ገንዘብን ለመቀበል ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።

መስክ ለቢትኮይን ትኩረት በሰጠበት ወቅት ቴስላ ሌሎች ተግዳሮቶችም እየገጠሙት ነው ፡፡

ኩባንያው ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸውን መኪኖች ለማሻሻል በማሰብ የመኪኖቹን ሽያጭ በቅርቡ አቁሟል። ከዚህ በተጨማሪም፤ በዚህ ወር መጀመሪያ የቻይና ተቆጣጣሪዎች የባትሪ ቃጠሎ እና ያልተለመደ የፍጥነት ሪፖርት ከተደረገ በኋላ በደህንነት እና በጥራት ጉዳዮች ላይ ድርጅቱን አነጋግረዋል። እነዚህም ምክንያቶች የቴስላን ገቢ ከቀነሱ ጉዳይ መካከል ተጠቅሰዋል።

እንደ ጄኔራል ሞተርስ እና ቮልስዋገን ያሉ ተፎካካሪ መኪና አምራቾችም በቅርብ ወራት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ትኩረታቸውን አጠናክረዋል።

እነዚህ ተግዳሮቶች የመጡት የቴስላ የአክሲዮን ዋጋዎች ከ 90 ዶላር ወደ 700 ዶላር በላይ በመመንደግ አስገራሚ ጭማሪን ካስከተሉ በኋላ የመጡ ናቸው።

ጭማሪዎች መስክ በጥር ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም የሐብታሞች ዘውርዝር የአማዞኑን ባለቤት ጄፍ ቤዞስን እንዲበልጥ አስችለውት ነበር።