ታይገር ዉድስ ባጋጠመው የመኪና አደጋ እግሮቹ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል ተባለ

እውቁ የጎልፍ ስፖርት ተጫዋጭ ታይገር ዉድስ በሎስ አንጀለስ የመኪና አደጋ አጋጥሞት ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

ውድስ "እግሮቹ ላይ ብዙ ጉዳት ስለደረሰበት" የቀዶ ህክምና እየተደረገለት ይገኛል ተብሏል።፡

የሎስ አንጀለስ ፖሊስ እንዳስታወቀው ታይገር ዉድስ የነበረበት ተሽከርካሪው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

የ15 ጊዜ የጎልፍ ሻምፒዮኑ እና የ45 ዓመቱ ዉድስ አደጋ ከደረሰበት መኪና በእሳት አደጋ ሰራተኞች እና በሕኪሞች ርብርብ ሊወጣ ችሏል።

ፖሊስ እንዳለው በአደጋው ስፍራ ዉድስ "እራሱን ያውቅ" ነበር ብሏል።

አሜሪካዊው በአምቡላንስ ዌስት ካርሰን ካሊፎርኒያ ወደሚገኘው ሃርበር-ዩሲኤልኤ የህክምና ማዕከል ተወሰዷል።

የዉድስ ወኪል ማርክ ስቲንበርግ ማክሰኞ ዕለት አደጋውን መድረሱን አረጋግጦ ቀዶ ጥገና እየተደረገለት እና ጉዳቱን በተመለከተ ዝርዝሩን ገልጿል።

የሎስ አንጀለስ የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል ኃላፊ ዳሪል ኦስቢ እንዳሉት "በሁለቱም እግሮች ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ተረድቻለሁ። ህይወቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ጉዳቶች አይደሉም" ብለዋል።

ቪላኑቫ እንዳሉት የውድስ መኪና "የመንገድ ማካፈያውን አቋርጦ ብዙ መቶ ሜትሮች ርቆ ሄዷል። ይህም ከመደበኛው ፍጥነት በላይ ይጓዝ እንደነበር ያመላክታል" ብለዋል።

አክለውም "አካባቢው ቁልቁል፣ ተዳፋት እና ጠመዝማዛ ስለሆነ ተደጋጋሚ አደጋዎች ይደጋገሙበታል" ሲሉ ገልጸዋል።

ዉድስ ያሽከረክረው የነበረው ቅንጡ መኪና የመንገድ ጠርዝ እና ዛፍ መግጨቱን እና ብዙ ጊዜ መገልበጡን ተናግረዋል።

የሎስ አንጀለስ ፖሊስ መምሪያ ምክትል ኃላፊ ካርሎስ ጎንዛሌዝ ቀድመው በቦታው ተገኝተው እንደነበር እና ዉድስ የደህንነት ቀበቶውን አጥልቆ እንደነበረና ስሙን ሲናገር "ረጋ ያለ እና ጥሩ ሁኔታ ላይ" ነበር ብለዋል።

አክለውም ዉድስ ከዚህ አደጋ በሕይወት ለመውጣት መቻሉ በጣም ዕድለኛ ነው ብለዋል።

በርካቶች ታይገር ዉድስ በፍጥነት ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም ምኞታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ዉድስ በጎርጎሮሳዊያኑ በ 2009 የመኪና አደጋ የደረሰበት ሲሆን በትዳሩ ላይ ታማኝ አለመሆኑን በማመኑ ትዳሩ ፈርሷል። ከጎልፍ ውድድር እረፍት ቢወስድም ብዙም ሳይቆይ ወደ ስፖርቱ ተመልሷል።

በ2013 ያስመዘገባቸው አምስት ድሎችን ተከትሎም ዉድስ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ውስጥ በጀርባ ህመም እና በከባድ ቀዶ ጥገናዎች ምክንያት 24 ውድድሮች ላይ ብቻ ተሳትፏል።

ዉድስ እአአ በ2017 ተሽከርካሪው ውስጥ ተኝቶ የተገኘ ሲሆን በዕጽ ተፅዕኖ ስር ሆኖ በማሽከርከር ተጠርጥሮ ነበር። በኋላም በግዴለሽነት ማሽከርከር ወንጀል ጥፋተኛ ተባሏል።

ዉድስ አምስተኛ የጀርባ ቀዶ ጥገናውን ተከትሎ በሚያዝያ ወር በሚካሄደው የማስተርስ ውድድር ለመሳተፍ ተስፋ እንዳደረገ ተናግሮ ነበር። በ2019 በጎልፍ የዓለም ደረጃ ስድስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ዉድስ አሁን ግን 50ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።