ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በ22 ሳምንቷ የተወለደችው ህፃን ከሆስፒታል ወጣች
መወለድ ከሚገባት ጊዜ አራት ወራት ቀደም ብላ ይህችን ምድር የተቀላቀለችው ህፃን ከሆስፒታል ወጣች።
በስኮትላንድ ኤርዲሪ ከተማ የተወለደችው ህፃን ሶፊያ፤ ከአንድ ወፈር ያለ ዳቦ የበለጠ አትመዝንም ነበር።
ሶፊያ ስትወለድ 500 ግራም የምትመዝን ሲሆን በእናቷ ማህፀን የቆየችው 22 ሳምንታትና አራት ቀናት ብቻ ነው።
እናቷ በነበራት የምጥ ወቅት ሶፊያ የመትረፍ እድሏ 10 በመቶ ብቻ እንደሆነ ተገምቶ ነበር።
ሶፊያ ጥር 24፣ 2013 ነበር ትወለዳለች ተብላ የተጠበቀችው።
እርሷ ግን ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ከጊዜዋ ቀድማ ከተፍ አለች።
ከጊዜዋ አራት ወራትን ቀድማም መስከረም 22 ይህችን ምድር ተቀላቀለች።
ስትወለድ በሕይወት ለመቆየቷ የተሰጠው ግምት አነስተኛ ነበር።
ሶፊያ አራት ወራትን ስኮትላንድ ውስጥ በሚገኘው ዊሻው ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል አሳልፋለች።
በዚያም የሕክምና ድጋፍ ተደርጎላት፤ በሕይወት ለመቆየት ችላ ከልዩ የሕክምና መስጫ ክፍል ወጥታለች።
በወላጆቿ እቅፍም ወደ ቤት እንድትሄድ ተደርጋለች።
ሶፊያ ይህ ዕድሜዋ በስኮትላንድ በሕይወት የሚገኝ ትንሽ ዕድሜ ያላት ሰው ሳያድርጋት እንዳልቀረ ይገመታል።
እናቷ ኢጌጃና አባቷ ኢንራስ፤ ኢጌጃ "132 ረጅምና ፈታኝ ቀናት" ያለችውን ጊዜ ከሳለፉ በኋላ ልጃቸውን ይዘው ወደ ቤት ሄደዋል።
የሶፊያ እናት የትውልድ አገሯ ላቲቪያ ቢሆንም በስኮትላንድ 12 ዓመታት ኖራለች።
ስለተፈጠረው ስትናገረም "እስከ 20ኛ የእርግዝና ሳምንቴ ድረስ ሁሉም ነገር መልካም ነበር። ከሳምንት በኃላ ግን ህመም ሲሰማኝ ወደ ሆስፒታል ሄድኩ። ወደ ምጥ እየተቃረብኩ እንደሆነም ተነገረኝ።" ትላለች።
ሆስፒታል አልጋ ከያዘች ከ10 ቀናት በኃላም ሶፊያ ተወለደች።
ሶፊያ ወደዚህ ዓለም ስትመጣ በከፋ ጩኸትና በመረረ ለቅሶ እንደነበርም ታስታውሳለች።
"ትተርፋለች ብለን አልጠበቅንም ነበር። ሆኖም የሕይወታችን ጉዞ ከዚህ ጀመረ።" ትላለች አጌጃ።
"እጅ ነበር የምታክለው"
ስትወለድ 500 ግራም ትመዝን የነበረችው ሶፊያ፤ ቁመቷ 26 ሴንቲ ሜትር ነበር።
የአንድ አዋቂ ሰው እጅ ነበር የምታክለው። ሶፊያ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ወራት በልዩ ሙቀት መስጫ ውስጥ ስታሳልፍ ወላጆቿ ጭንቀት ውስጥ ነበሩ።
"ያለማጋነን የአዋቂ እጅ ነበር የምታክለው። በቀላሉ የምትጎዳም ዓይነት ነበረች። በቆዳዋ ውስጥም ሰውነቷ ይታይ ነበር። ልጄን ለማቀፍ አንድ ሳምንት ቆይቻለው።" ብላለች ኢጌጃ።
ሶፊያ የልብ ችግር፣ የአንጎል ደም መፍሰስ፣ የዓይን ህመምና በርካታ ኢንፌክሽኖች የነበረባት ቢሆንም፤ አሁን ግን ጤናዋ ተመልሷል።
ሳምባዋም ቢሆን በሚገባ ያልዳበረ በመሆኑ ለመተንፈስ ትቸገር ነበር።
በዚህም ምክንያት በመተንፈሻ መሳሪያ ለመታገዝ ተገዳለች።
አሁን ከሆስፒታል ወጥታ ወደ ቤት ብትሄድም ተጨማሪ ኦክስጅን እንድታገኝ አነስተኛ ተቦ ተደርጎላታል።
የሶፊያ እናት ኢጌጃ "ሁሉንም ጊዜ ሆስፒታል ነበር ያሳለፍኩት። አንዳንድ ቀን እስከ 16 ሰዓታት የምቆይበት ጊዜ ነበር። ባለቤቴ ከሥራ በኃላ ይመጣ ነበር። በተለይ በእነዚያ አስቸጋሪ ወቅቶች ከእርሷ መለየት አልፈልግም ነበር" ስትል ያሳለፈችውን ገልጻለች።
"ብዙ የሕክምና መሳሪያዎች ተገጥመውላት ነበር። መጀመሪያ ላይ በራሷ እንድትተነፍስ ተሞክሮ ነበር። 20 ደቂቃ ከቆየች በኃላ የልብ ምቷ መውረድ ጀመረ። ያጣኋት ነበር የመሰለኝ። ግን የሕክምና ባለሙያዎቹ አስደናቂ ነበሩ።" ስትልም ለልጇ የተደረገላትን የሕክምና እርዳታ አሞግሳለች።
የሶፊያ ውብ ፈገግታ
ሶፊያ ያለመተንፈሻ መሳሪያ እንድትተነፈስ በሳምንታት ውስጥ ስድስት ጊዜ ተሞክሯል።
ሶፊያ እየጠነከረችና ክብደቷም እየተሻሻለ የመጣው ግን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ነበር።
በመጨረሻም ከሆስፒታል መውጫዋ ጊዜ ደረሰ።
የሶፊያ እናት።"ወደ ቤት ከሄድን ጀምሮ ሶፊያ መልካም ሁኔታ ላይ ትገኛለች። ፊቷ ላይ በጣም ውብ ፈገግታ ይነበባል። አዲሱንም አካባቢ እየተላመደችው ነው። ከተወለደች አራት ወር ተቆጥሯል። እያየኋት አሁንም ማህፀኔ ውስጥ እንደሆነች አስባለው። ምክንያቱም ከተወለደችበት ክብደት በአራት እጥፍ ብትልቅም አሁንም በጣም ትንሽ ናት።" ስትል ሶፊያ አሁን ስላለችበት ሁኔታ ገልጻለች።
ሶፊያ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ቋሚ የሕክምና ክትትል ማድረግ ይኖርባታል።
ለሦስት ወይም ለአራት ዓመታት ደግሞ በሳንባ ክሊኒክ መታየት ይኖርባታል። እድገቷ ግን በትክክለኛ መንገድ እየተጓዘ ነው ተብሏል።
ኢጌጃ " በዚህ አይነት ሁኔታ የምታልፉና ምጥ ቀድሞ የሚመጣባችሁ እናቶች ተስፋ አለ። በፍፁም ተስፋ አትቁረጡ" በማለትም መክራለች።
የሆስፒታሉ ዋና አዋላጅ ቼራል ክላርክ በበኩሏ "የህፃኗ ሳፊያ የሕክምና ሂደት መነሳሳትን የሚፈጥር ነው። አሁን ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ ቤቷ በመሄዷ በጣም ደስተኛ ነኝ።" በማለት፤ በዚህ ሂደት ውስጥ በተሳተፉ የሕክምና ባለሙያዎች ስም ለሶፊያና ለወላጆቿ መልካም ምኞቷን ገልጻለች።