ውሻዋ የአሳዳጊዋን ሀብት ወርሳ ሚልየነር ሆነች

ይህች ውሻ ሚሊየነር ናት። ገንዘቡን ያገኘችው ቀን ተሌት ሰርታ ለፍታ አይደለም፣ ያለ ስስት ብዙ ፍቅር ለባለቤቷ በመስጠቷ ገንዘቡን ወርሳ ነው።

አሳዳጊዋ 5 ሚሊዮን ዶላር በውርስ ትቶላት ወደ ማይቀረው ዓለም ሄዷል፤ ሞቷል።

የውሻዋ ስም ሉሉ ይባላል። አሳዳሪዋ የነበረው ግለሰብ ደግሞ የናጠጠ ሃብታም የነበረው ቢል ዶሪስ ነው።

በናሽቪል ቴኔሲ የምትኖረው ሉሉ ስምንት ዓመቷ ሲሆን ባለፈው ዓመት ቢል ዶሪስ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ተናዝዞላታል።

ማርታ በርተን የዶሪስ ጓደኛ የነበረች ስትሆን አሁን ደግሞ የሉሉ ቋሚ ተንከባካቢ ነች።

ስለ ሁኔታው ስትጠየቅም "እውነቱን ለመናገር ምን እንደሚሰማኝ ለማወቅ አልችልም" ብላለች።

በአንድ ነገር ግን እርግጠኛ ናት፤ ቢል ከመሞቱ በፊት ለውሻው ሉሉ ብርቱ ፍቅር ነበረው።

እጅግ የበረታ፤ ከብረት የጠነከረ ማለት ይቻላል።

ቢል ባስቀመጠው ኑዛዜ ላይ በየወሩ በርተን ሉሉን ለመንከባከብ ያወጣችው "ምክንያታዊ ወጪ" እየተሰላ እንዲከፈላት ይላል።

እንዲህ ሚሊየኖች በኑዛዜ የተተወላት ሉሉ ምን ዓይነት ውሻ ብትሆን ነው?

"መልካም ጠባይ ነው ያላት" ትላለች በርተን።

በርተን 5 ሚሊዮን ዶላሩንም ሉሉን ለመንከባከብ መንዝራና ዘርዝራ የምትጨርሰው ይመስላት ይሆን?

"እንግዲህ መቼስ ምን ይደረጋል፤ እሞክራለኋ" ሳቅ የታጀበ የእርሷ መልስ ነበር።

ሉሉ እንደ ባለቤቷ ዶሪስ ወደማይቀርበት ዓለም ብትሄድ፣ ከወጪ ቀሪ የሚተርፋት ገንዘብ ምን እንደሚሆን የታወቀ ነገር የለም።

እኤአ በ1992 እንዲህ እንደ ሉሉ እድለኛ የነበረ ውሻ 80 ሚሊዮን ዶላር መውረሱ የተዘገበ ሲሆን፤ በ2002 ደግሞ ማይለስ ብላክዌል የተባለ ደራሲ ጊጉ ለተሰኘች ዶሮው 15 ሚሊዮን ዶላር እስካለሽ ድረስ ተምነሽነሺበት በሚል ተናዝዞላታል።

ባልበላውም ልበትነው ብላ ካላባከነችው በቀር እርሷስ ያን ያህልም አትፈጅ!