ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሚየንማር ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡት መካከል አንዲት ሴት እንደተተኮሰባት ተገለጸ
ወታደራዊው ኃይል በሚየንማር መሪ ላይ ያደረገውን መፈንቅለ መንግሥት ለማውገዝ አደባባይ ከወጡ ዜጎች መካከል አንዷ በጥይት ተመትታ ክፉኛ መጎዳቷ ተነግሯል።
ማክሰኞ በተካሄደው ሰልፍ ፖሊስ ተቃዋሚዎቹን ለመበተን ውሃ እና አስለቃሽ ጭስ ተጠቅሞ ነበር። የመብት ተሟጋች ቡድኖች እንደሚሉት ጉዳት የደረሰባት ሴት የተመታችው ራሷ ላይ ሲሆን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
እስካሁን በይፋ የተነገረ ሌላ ጉዳት ስለመኖሩ ባይገለጽም ፖሊስ ኃይል መጠቀሙ ግን እየተዘገበ ነው።
መፈንቅለ መንግሥቱ ከተደረገ በኋላ በብዛት መሰባሰብ እና የሰዓት እላፊ እወጃ በአገሪቱ ቢጣልም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የሚየንማር ዜጎች ግን በመዲናዋ ናይ ፒይ ታው አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ዛሬ አምስተኛ ቀኑን በያዘው የሚየንማር ተቃውሞ ከተለያዩ የሲቪል ሠራተኞች የተሰባሰቡ ሰዎች አምስተኛውን ቀንም በተቃውሞ ለማሳለፍ ከማለዳው በመዲናዋ ተገናኝተዋል።
ማክሰኞ ምንድን ነው የሆነው?
ተቃውሟቸውን በቀጠሉ ዜጎች ላይ ፖሊስ ሰልፉን ለመበተን በሚል ውሃ ተጠቅሟል።
አስለቃሽ ጭስ ከመተኮሱ በፊትም ፖሊስ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ወደ ሰማይ ይተኩስ ነበር።
ነገር ግን ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ ያነጋገሯቸው ተጎጂዎችን ያከሙ ሃኪሞች ፖሊስ በተቃዋሚዎች ላይ ጥይት ሳይተኩስ እንዳልቀረ ተናገግረዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው ሌላ አንድ ሃኪም አንዲት ሴት በጥይት ጭንቅላቷ ላይ የተመታች ሲሆን አንድ ሌላ ሰው ደግሞ በተመሳሳይ ደረቱ ላይ በጥይት ተመትቷል ብለዋል።
ሂውማን ራይትስ ዎች እና ሌሎችም የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ሴትዮዋ በጥይት መመታቷን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የማክሰኞው የፖሊስ ጥቃት እጅግ አሳስቦኛል ብሏል።
በሚየንማር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ ኦላ አልምግሬን "በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ያልተመጣጠነ ኃይል መጠቀም ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።
በአገሪቱ ከፈረንጆቹ 1988 እስከ 2007 ድረስ በነበረው ወታደራዊ አስተዳደር ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን መግደል የተለመደ ነበር።
ወታደሩ ማክሰኞ ምሽት የሳን ሱ ቺን ፓርቲ ጽህፈት ቤት ቤት መውረሩና ማውደሙ ተገልጿል።
በስፍራው የሚገኘው ቢቢሲ በርማም ይህንን አረጋግጧል። ወታደሩ ተቃዋሚዎችን በመደገፍ ምርጫው ተጭበርብሯል እንደገና መካሄድ አለበት የሚል አቋም ሲያንጸባርቅ ቆይቷል።
የምርጫ ኮሚሽን ደግሞ ምርጫው ስለመጭበርበሩ የሚያስረግጥ አንዳችም ማስረጃ የለም ብሏል። መፈንቅለ መንግሥቱ አዲስ የፓርላማ አባላትን ለማዋቀር ያለመ ነው ብሏል።
የቀድሞዋ መሪ ሳን ሱ ቺ በቁም እሥራት ላይ የሚገኙ ሲሆን በሕገ ወጥ መንገድ የገባ የግንኙነት መሣሪያን በመያዝ ተከስሰዋል። ሌሎች በርካታ የእርሳቸው ፓርቲ አባላትም ታስረዋል።