ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕንድ የበርድ ፍሉ ወረርሽኝን በመፍራት ዶሮዎችን ማስወገድ ጀመረች
ሕንድ በመላው አገሪቱ የዱር ዝይ፣ ቁራዎች እና ዳክዬዎች ላይ 'አቪያን ፍሉ' የተሰኘው በሽታ ከተገኘባቸው በኋላ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዶሮዎችን ማስወገድ ጀምራለች።
ባለሥልጣናት ኤች5ኤን8 ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ መኖሩን ያወቁት ከሳምንት በፊት የወፍ መንጋዎች በተለያዩ ግዛቶች ሞተው ከተገኙ በኋላ ነው።
የፌደራል መንግሥቱ ስርጭቱን ለመግታት "አስቸኳይ እርምጃዎችን" እንዲወስዱ "ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ" አውጥቷል።
አብዛኞቹ ዝርያዎች ለሰው ልጆች ያላቸው ተጋላጭነት ዝቅተኛ ቢሆንም ሰዎች የሞቱ ወይም የታመሙ ወፎች እንዳይነኩ ተመክረዋል።
ሕንድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች በምትገኝበት ወቅት ነው ይህ የበሽታ ስጋት መኖሩ የተገለጸው።
አገሪቱ በጥቂት ወራቶች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመከተብ የሚያስችል ከፍተኛ የክትባት ፕሮግራም ለመጀመር በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
በአንዳንድ አካባቢዎች የዶሮ መሸጫ ሱቆችም የተዘጉ ሲሆን የእንቁላል ሽያጭም ተቋርጧል።
ቫይረሱ ሌሎች የአዕዋፍ ዝርያዎችንም አዳርሷል።
በሰሜናዊው የሂማቻል ፕራዴሽ ግዛት ወደ 2,400 የሚፈልሱ ወፎች በፖንግ ግድብ ሐይቅ አካባቢ ሞተው ተገኝተዋል ሲሉ የእንስሳት በሽታ ባለሙያ የሆኑት ቪክራም ሲንግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በግድብ 10 ኪ.ሜ አካባቢ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። በዚህ አካባቢ የዶሮ እርባታ ባለመኖሩ እስካሁን ድረስ በዶሮ እርባታ ውስጥ ምንም የወፍ ጉንፋን ምልክቶች አልተገኙም" ብለዋል።
ባለሥልጣናት በደቡባዊ ኬራላ እስከ 12,000 የሚደርሱ ዳክዬዎች መሞታቸውን የገለጹ ሲሆን በክልሉ መመሪያ መሠረት ከ36,000 በላይ ወፎችን ለማስወገድ መታቀዱን አስታውቀዋል።
በማድያ ፕራዴሽ ማዕከላዊ ግዛት ባለፉት 10 ቀናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ቁራዎች መሞታቸው ተገልጻል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሽመላዎች እና ርግቦች እንደሞቱም ሪፖርት ተደርጓል።
በኢንዶሬ ከተማ 50 ቁራዎች ሞተው ሲገኙ ባለስልጣናት በአቅራቢያው ካሉ ነዋሪዎች መካከል እንደብርድ፣ ሳል እና ትኩሳት ያሉ ምልክቶችን ያለባቸውን በመፈለግ ላይ ናቸው።
ባለሥልጣናቱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በክልሉ ሁኔታውን ለመቋቋም የቁጥጥር ሥራ የሚያከናውን ክፍል ተቋቁሟል።