ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሥነ -ምግብ፡ ህጻናት በአመጋገብ ምክንያት ቁመታቸው በ20 ሴንቲ ሜትር ሊያጥር ይችላል
ህጻናት በአመጋገብ ምክንያት ቁመታቸው በ20 ሴንቲ ሜትር ሊያጥር እንደሚችል ተጠቆመ።
በደካማ የአመጋገብ ስርዓት ምክንያት ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሱ ሕፃናት መካከል የ20 ሴ.ሜ አማካይ የቁመት ልዩነት እንዲኖር አስተዋፅዖ ሊያበረክት ይችላል ተብሏል።
በ2019 ጥናት ረዣዥሞቹ የ19 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወንዶች በኔዘርላንድስ (183.8 ሴ.ሜ ) ሲኖሩ እና አጭሩ ደግሞ በቲሞር ሌስቴ (160.1ሴ.ሜ) እንደሚኖር ተዘግቧል።
ጥናቱ በዘ ላንሴት የሕክምና መጽሔት ነው ይፋ የተደረገው።
እንደ ተመራማሪዎቹ ከሆነ በዓለም ዙሪያ በህፃናት ቁመት እና ክብደት ላይ የታዩ ለውጦችን መከታተል የሚመገቡትን የተመጣጠነ ምግብ እና አካባቢያቸው ምን ያህል ጤናማ ነው የሚለውን ለማወቅ ስለሚረዳ አስፈላጊ ነው።
የምርምር ቡድኑ እ.አ.አ ከ1985 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ2000 በላይ ጥናቶች የተካተቱ ከ5 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ከ65 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን እና ታዳጊዎችን መረጃ ተንትኗል።
በ2019 በሰሜን-ምዕራብ እና በመካከለኛው አውሮፓ (ለምሳሌ በኔዘርላንድስ እና በሞንቴኔግሮ ያሉ) ሕፃናት እና ታዳጊዎች በዓለም ላይ በአማካይ ረዥሞች መሆናቸውን ለማወቅ ችለዋል።
በአማካይ አጫጭር የሆኑት የ19 ዓመት ዕድሜ ወጣቶች ደግሞ በደቡብ እና በደቡብ ምስራቅ እስያ፣ በላቲን አሜሪካ እና በምስራቅ አፍሪካ ይኖራሉ።
እ.ኤ.አ. በ2019 ትንታኔ እንደሚያመለክተው፦
- በላኦስ የ19 ዓመት ወንዶች በኔዘርላንድስ ካሉ የ13 ዓመት ካላቸው ወንዶች ጋር ተመሳሳይ ቁመት (162.8 ሴ.ሜ ) ነበራቸው።
- 19 ዓመት የሆናቸው የጓቲማላ፣ ባንግላዴሽ፣ ኔፓል እና ቲሞር ሌስቴ ያሉ ሴቶች አማካይ ቁመት ከ11 ዓመት የደች ሴት አማካይ ቁመት (152 ሴ.ሜ) ጋር ተመሳሳይ ነው።
- ባለፉት 35 ዓመታት ውስጥ በልጆች አማካይ ቁመት ትልቁ መሻሻል በቻይና እና በደቡብ ኮሪያ ተመዝግቧል።
- ከ1985 ጀምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች አማካይ ቁመት አልተለወጠም ወይም ሲቀንስ ቆይቷል።
ጤናማ ክብደት ያለው ትርፍ
ጥናቱ ከዚህ በተጨማሪም የህፃናቱን ቁመት ካላቸው ክብደት ጋር ያለው ምጥጥን (ቢኤምአይ) ጤናማ ስለመሆን አለመሆኑም ተመልክቷል።
እንደ ተመራማሪዎቹ ትልቁ ቢኤምአይ ያላቸው ታዳጊዎች በፓስፊክ ደሴቶች፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአሜሪካ እና በኒው ዚላንድ ይኖራሉ።
በጣም ዝቅተኛ ቢኤምአይ ያላቸው የ19 ዓመት ወጣቶች የሚኖሩት እንደ ሕንድ እና ባንግላዴሽ ባሉ የደቡብ እስያ አገሮች ውስጥ ነው።
በጥናቱ በጣም ዝቅተኛ እና ከፍተኛ ቢኤምአይ ባሉባቸው ሀገሮች መካከል ያለው ልዩነት 25 ኪ.ግ ገደማ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
በአንዳንድ አገሮች ሕፃናት በአምስት ዓመታቸው ጤናማ ቢኤምአይ ቢኖራቸውም ዕድሜያቸው 19 ዓመት ሲሆን ከመጠን በላይ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው።