የቤልጂየም ሀኪሞች በኮሮናቫይረስ ቢያዙም ሥራ እንዲቀጥሉ ተነገራቸው

የቤልጂየም ሀኪሞች በኮሮናቫይረስ ቢያዙም ሥራ እንዲቀጥሉ ተነገራቸው። በወረርሽኙ ተይዘው ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ነው ይህ ውሳኔ የተላለፈው።

ሊዮግ በተባለ ከተማ አንድ አራተኛው የህክምና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል። 10 ሆስፒታሎች ሀኪሞች በቫይረሱ ቢያዙም የበሽታው ምልክት ካልታየባቸው ሥራ እንዳያቋርጡ ወስነዋል።

የቤልጂየም ሀኪሞች ማኅበር ኃላፊ ዶ/ር ፊሊፔ ዴቮስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ሆስፒታሎች በቀናት ውስጥ አገልግሎት መስጠት ሊያቆሙ ስለሚችሉ የህክምና ባለሙያዎች በቫይረሱ ቢያዙም ሥራ ከመቀጠል ውጪ አማራጭ የላቸውም።

ሀኪሞች በሽታውን ወደ ታካሚዎች የሚያስተላልፉበት እድል ሊኖር እንደሚችል ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በምሥራቅ ቤልጂየም በሚገኘው ከተማ ከሦስት ሰዎች አንድ ሰው ላይ ቫይረሱ ይገኛል። ታማሚዎች ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች እየተዘዋወሩ ሲሆን፤ አጣዳፊ ያልሆነ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ደግሞ ቀጠሯቸው ወደ ሌላ ጊዜ ተዘዋውሯል።

የጤና ሚንስትሩ ፍራንክ ቫንደንብሮክ አገሪቱ በወረርሽኙ ክፉኛ ልትጎዳ እንደምትችል እና ከዚህ በኋላ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት አመራሮች እንዳሉት፤ በአህጉሪቱ የጉዞና ከቤት ያለመውጣት ገደብ ሊያስፈልግ ይችላል።

የድርጅቱ የድንገተኛ ጊዜ ኃላፊ ዶ/ር ማይክ ራየን "አሁን ላይ አውሮፓ ውስጥ ቫይረሱን ለመቆጣጠር እርምጃዎችን ማጥበቅ ያስፈልጋል" ብለዋል።

መጋቢት ላይ በወረርሽኙ ክፉኛ የተጎዳችው ጣልያን ቴአትር ቤቶች፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ እና መዋኛ ስፍራዎችን ዘግታለች።

ሬስቶራንቶች እና ካፌዎች ከ12 ሰዓት በኋላ የመስተንግዶ አገልግሎት መስጠት አይችሉም።

እስከ ጥቅምት 24 በሚቆየው መመሪያ መሠረት፤ 75% የሁለተኛ ደረጃ እና ዩኒቨርስቲ ትምህርቶች በድረ ገጽ ይሰጣሉ።

በተጨማሪም ዜጎች እጅግ አስፈላጊ ካልሆነ ከከተማ ከተማ እንዳይዘዋወሩ ተነግሯቸዋል።

በእርግጥ ይህን አዲስ መመርያ በመቃወም በኔፓልስ፣ ቱሪን እና ሮም ከተሞች ሰልፍ ተካሂዷል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ የተዘጋው በጣልያን ብቻ ሳይሆን በቤልጄም መዲና ብራሰልስ ጭምርም ነው።

መደብሮች ከምሽቱ 2 ሰዓት እንዲዘጉ መመሪያ ተላልፏል። ሰው በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ ነው።

ዩኬ ውስጥ በወረርሽኙ ሳቢያ ከ16 እስከ 25 እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች ሥራቸውን የማጣት እድላቸው ከጎልማሶች በእጥፍ የበለጠ ሆኗል።

በሌላ በኩል ፈረንሳይ ውስጥ በየቀኑ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ደ100,000 ደርሰዋል። ይህም የበሽታውን ምልክት የማያሳዩና ህክምና ያልተሰጣቸውን ሰዎች እንደሚያካትት የአገሪቱ የሳይንስ ካውንስል ኃላፊ ፕ/ር ጀን ፍራንኮስ ደልፍረሲ ተናግረዋል።

ሌላዋ የአውሮፓ አገር ቼክ ሪፐብሊክ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥላለች። ለህክምና ወይም ለሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ ካልሆነ ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 11 ሰዓት ድረስ ከቤት መውጣት አይቻልም።

መደብሮች ከ2 ሰዓት በኋላ አገልግሎት መስጠት የሚያቆሙ ሲሆን፤ ዘወትር እሑድ ይዘጋሉ።

ሌላ በኩል ስፔን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጋለች። የሰዓት እላፊ ገደብም ተጥሏል።

ጠቅላይ ሚንስትር ፔድሮ ሳንቼዝ እንዳሉት ሰዓት እላፊው ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ንጋት ይቆያል።

የተለያዩ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች ጉዞ የማገድ ሥልጣንም ተሰጥቷቸዋል።

ሩስያ ውስጥ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 17,347 መድረሱ ተገልጿል። አጠቃላይ በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች 1.5 ሚሊዮን ደርሰዋል።