ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኦሮሚያ፡ የኦሮሚያ አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ "የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው" አለ
ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው አለመረጋጋት ለመቆጣጠር የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
በኦሮሚያ ለተቃውሞ በተጠሩ ሰልፎች ምክንያት የሰዎች ህይወት መጥፋቱን ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች "ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል" ከመጠቀም እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
በክልሉ በአሳሳ፣ አሰቦት፣ አወዳይ፣ ባሌ ሮቤ፣ ጭሮ፣ ደንገጎ፣ ድሬ ጠያራ፣ ዶዶላ፣ ገለምሶ፣ ጊኒር፣ ሀሮማያ፣ ሂርና እና ሻሸመኔ ባሉ ከተሞች የሰዎች ህይወት ማለፉን ኮሚሽኑ ከተለያዩ ምንጮች መረጃ እንደደረሰውም በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
የሰዎች ህይወት ያለፈውም የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ በተጠራ የተቃውሞ ሰልፍ መሆኑንም ጠቅሷል።
በኦሮሚያ ክልል የአስተዳርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጂብሪል መሐመድን ስለተፈጠረው አለመረጋጋትና በጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ተወስዷል መባሉን አስተባብለዋል።
"ኮሚሸኑ ያወጣው መግለጫ ብዙ ስህትት አለው" ያሉት አቶ ጂብሪል መግለጫው "ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ሰዎች ላይ" ማለቱን በማንሳት ሰላማዊ ሰልፍ የሚባል ነገር እንደማያውቁ ገልፀዋል።
እንደ አስተዳደርና ጸጥታ ኃላፊው የተካሄደው "ሁከት" ነው። ሁለተኛው ስህተት ይላሉ አቶ ጂብሪል፣ "ሰልፍ የወጡ ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ይፈቱ ይላሉ። የፓርቲ አመራር ስለሆነ የታሰረ የለም። በወንጀል ስለተጠረጠሩ ነው የታሰሩት" ሲሉ ያስረዳሉ።
በሶስተኝነትም መግለጫውን ለማስተባበል የጠቀሱት "ምንጫቸው ፌስቡክ ነው። ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል ምላሽ አልጠየቁም" የሚል ነው።
የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ አይደለም የሚለውን ክስ ሲመልሱ "ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ከተወሰደ ማየት ይቻላል። እስካሁን ባለው የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው።" ብለዋል።
አቶ ጂብሪል የተደረገው ነገር ሰላማዊ ሰልፍ ሳይሆን ሁከት ነው ካሉ በኋላ፣ የመንገድ የመዝጋት ሙከራ፣ ንብረት ለመዝረፍ፣ የትራንስፖርት መስጫ ተሽከርካሪዎችን ለመሰባበር፣ መንገደኞች ላይ ጠርሙስ ውስጥ ቤንዚን ጨምሮ ክብሪት ለኩሶ ለማቃጠል መሞከሩን እና ባንክ ለመዝረፍ የተሞከረበት ቦታም መኖሩን ገልፀዋል።
በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ይላሉ የኦሮሚያ አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊው፣ "መኪና ሁሉ ተጓዥ 30 ሰው ከሚሞት አንድ ሰው መሞቱ ግድ ይላል። እንደዚህ አይነት እርምጃ ነው የተወሰደው። ይህም ይቀጥላል።"
ዶዶላ የቆሰለ ፖሊስ፣ የሞተ የመንግሥት ካቢኔ አባል አለ ያሉት አቶ ጂብሪል፣ የገደለው ሰውዬ እንዲቆም ተነግሮት እምቢ በማለቱ ፀጥታ ኃይሎች እርምጃ መውሰዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አክለውም "ይህ ሲሆን እንደዚህ አይነት እርምጃዎች የማይወሰዱ ከሆነ የሕግ የበላይነት የሚባለው የት አለ ታዲያ?" ሲሉ ጥያቄ ያቀርባሉ።
"ሐረር ላይ ከወታደር መሣሪያ ቀምቶ ከሌላው ሊቀማ ሲል ነው እርምጃ የተወሰደው። . . . በአጠቃላይ የሚጣራ ነገር ሊኖር ይችላል። አልፎ አልፎ ስህተት የተፈጸመባቸው ቦታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በመቶኛ ግን ስናየው አብዛኛው ቦታ የተወሰዱት እርምጃዎች ተመጣጣኝ ናቸው።"
የሞቱና የቆሰሉ ሰዎች ቁጥርን ተጠይቀውም፣ "መረጃ እየተጠናቀረ ነው። ሲያልቅ እንናገራለን" ብለዋል።
ከሰኞ እለት ጀምሮ በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች የሆነው ምንድን ነው?
በክልሉ በተለያዩ ከተሞች ከሰኞ ጀምሮ አለመረጋጋት መኖሩን መዘገባችን ይታወሳል። ሰኞ እለት በድሬ ጥያራ ከተማ የባለቤቷ ወንድም እንደተገደለ እና ትናንት ሥርዓተ ቀብሩ እንደተፈጸመ ለደህንነቷ ሲባል ስሟ ያልተገለፀ ወጣት ለቢቢሲ ተናግራናለች።
የሞተው ወጣት 30 ዓመቱ መሆኑን ገልፃ፣ በቅርቡ ያገባ ሙሽራ እንደነበር ነግራናለች። እርሱና ሶስት ጓደኞቹ በፀጥታ ኃይሎች በጥይት የተመታን ግለሰብ፣ በባጃጅ ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ላይ ሳሉ፣ ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች በማስቆም እንደ ደበደቧቸውና የአጎቷ ልጅም በጥይት ተመትቶ መሞቱን ትናገራለች።
በድሬ ጥያራ የሚሠሩ የጤና ባለሙያ ደግሞ "በ12 በነበረው ሰልፍ ላይ ከባድ ተኩስ ነበር። ሲተኮስ እኛ ጤና ጣቢያ ነበርን። ከዛ መከላከያዎች ወደ እኛ መጡና አስክሬን የምትሰበስቡበት አምቡላንስ ይዛችሁ ኑ አሉን" በማለት የተፈጠረውን ሁናቴ ያስታውሳሉ።
በቦታው በተገኙበት ወቅትም በርካታ ሰዎች በጥይት ተመትተው፣ ሌሎች ተደብድበው፣ ሌሎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፎ ሜዳ ላይ መመልከታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በሕይወት ለነበሩት እርዳታ ሰጥተን ወደ ሆስፒታል ሪፈር አደረግን። የሞቱትን ወደ ጤና ጣቢያው ወሰድን። ሁለት ልጆች ሞተዋል። አንደኛው ማዲ ኡመር ሁለተኛው ደግሞ ፈሪድ አብዲ ይባላል። በወቅቱ ተደብድበው የነበሩትን መቁጠር አልቻልኩም። በጥይት የተመቱት ግን ወደ 12 የሚሆኑ ሰዎች ናቸው" ሲሉ የተመለከቱትን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በጭሮ ሆስፒታል የጤና ባለሙያም ስላለው ሁኔታ ሲናገሩ "በቀደም [ሰኞ] 24 ሰዎች ተመትተው ነበር እኛጋ የመጡት። ከዛ በኋላ ቁጥሩ 30 ደርሷል" ካሉ በኋላ ሰኞ እለት ተመትቶ ወደ ጭሮ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት የነበረ ጉማ የሚባል የ19 ዓመት ወጣት ሐሙስ እለት ሕይወቱ ማለፉን ተናግረዋል።
". . .ሌላ ወጣት ዶባ ከሚባል ወረዳ በጥይት ተመትቶ መጥቶ ነበር። ትናንት ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል እየወሰድነው ሳለ ሞተ። በአጠቃላይ በኛ ሆስፒታል አራት ሰዎች ሞተዋል። አራቱም በጥይት ነው የተመቱት።"
በሐረር ሕይወት ፋና ሆስፒታል የሚሠሩ ባለሙያ እንደነገሩን ከሆነ ደግሞ፣ ከአወዳይና ከሌሎችም ከተሞች 23 ሰዎች ተመትተው ሆስፒታል ገብተዋል። ሦስት ሰዎች ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ እንደሞቱም ነግረውናል። ባለሙያው እንዳሉት አብዛኞቹ በሆስፒታላቸው የሚገኙት ሰዎች ጭንቅላታቸው እና ከጀርባቸው የተመቱ ናቸው። አብዛኞቹ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም አክለዋል።