የትራምፕ አስተዳደር የውጪ አገር ተማሪዎችን ወደ አገራቸው የመመለስ እቅድን ውድቅ አደረገ

የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ሳቢያ ትምህርታቸውን በበይነ መረብ አማካኝነት የሚከታተሉ የውጪ አገር ተማሪዎችን ወደ አገራቸው የመመለስ እቅድን ውድቅ ማድረጉ ተገለፀ።

እቅዱ ውድቅ የተደረገው ፖሊሲው ከተዋወቀ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር።

ባለፈው ሳምንት የውጪ አገር ተማሪዎች በአካል ቀርበው ትምህርታቸውን መከታተል የማይችሉ ከሆነ አሜሪካ ውስጥ እንዲቆዩ እንደማይፈቀድላቸው ተነግሯቸው ነበር።

በወረርሽኙ ሳቢያ መጋቢት ወር ላይ የትምህርት አጋማሽ አጠናቀው ወደ አገራቸው ተመልሰው የነበሩ ተማሪዎችም ትምህርታቸው በበይነ መረብ እየተሰጠ በመሆኑ ወደ አሜሪካ ለመመለስ አይፈቀድላችሁም ተብለው ነበር።

የአገሪቷ የስደተኞችና ጉምሩክ የሚመለከተው ኤጀንሲም በበኩሉ ሰዎች ይህንን ሕግ የማያከብሩ ከሆነ ወደ አገራቸው ተጠርንፈው እንደሚመለሱ ማስታወቁ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎም የማሳቹስቴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም እና ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መንግሥት ተማሪዎቹን ለመመለስ የያዘውን እቅድ ተከትሎ መንግሥትን ከሰው ነበር።

በማሳቹስቴትስ የዲስትሪክት ዳኛ አሊሰን ቡሮንስ በጉዳዩ ላይ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ስምምነቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት መጋቢት ወር ላይ ተግባራዊ የተደረገውና የውጭ አገር ተማሪዎች ትምህርታቸውን በበይነ መረብ እንዲከታተሉና በአገሪቷም ሕጋዊ ሆነው እንዲቆዩ መፈቀዱን ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

በየዓመቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጪ አገር ተማሪዎች ለትምህርት ወደ አሜሪካ ይጓዛሉ። ለዩኒቨርሲቲዎችም ከፍተኛ የሆነ ገቢ ያስገኛሉ።

ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ የቫይረሱ ሥርጭት መስፋፋቱን ተከትሎ ተማሪዎች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ወደ ትምህርት ገበታቸው ሲመለሱ ትምህርቱ በበይነ መረብ አማካኝት እንደሚሰጥ አስታውቋል። የማሳቹስቴትስ የቴክኖሎጂ ተቋምም ልክ እንደሌሎቹ የትምህርት ተቋማት በበይነ መረብ ትምህርት መስጠቱን እንደሚቀጥል ገልጿል።