ቱኒዚያዊቷ ፌስቡክ ላይ ባሰፈረችው ጽሁፍ የስድስት ወር እሰር ተፈረደባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቱኒዚያዊቷ ጦማሪ የኮሮናቫይረስን በተመለከተ ቅዱስ ቁርዓን በሚጻፍበት መንገድ ባሰፈረችው ምጸታዊ ጽሁፍ የተነሳ የስድስት ወር እስር ተፈረደባት።
የ28 ዓመቷ ወጣት ኤምና ቻርኪ ባለፈው ግንቦት ወር በፌስቡክ ላይ ሕዝቡ የኮሮናቫይረስ በሽታን ለመከላከል የንጽህና አጠባበቅ ደንቦችን እንዲከተል ባሰፈረችው መልዕክት ነው የተከሰሰችው።
ነገር ግን ኤምና መልዕክቷን የጻፈችው የእስልምና ቅዱስ መጽሐፍ ቁርዓን በሚጻፍበት መንገድ መሆኑ ነው የስድስት ወር እስር ያስፈረደባት።
ኤምና በቅርቡ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ ላይ እንዳለችው በዚህ መንገድ የጻፈችው ሰዎችን ለማስደንገጥ ሳይሆን መልዕክቱን ዘና የሚያደርግ እንዲሆን በማለት እንደሆነ ተናግራለች።
ለዚህ ድርጊቷም ፍርድ ቤት ቀርባ "በሐይማኖቶች መካከል ጥላቻን በመፍጠር" ጥፋተኛ ተብላ እስር ተወስኖባታል።
ነገር ግን ኤምና ይግባኝ ለመጠየቅ እያሰበች ስለሆነ አስካሁን እስር ቤት አልገባችም።
ኤምና በማኅበራዊ መገናኛ መድረክ ላይ ባሰፈረችው ጽሑፍ የቅዱሱ መጽሐፍ አንቀጾች በተጻፉበት መንገድ መሆኑ እንጂ ይዘቱ የጤና መልዕክት እንደሆነ ነው የተገለጸው።
የጽሑፉ ይዘት ሕዝቡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እጁን እንዲታጠብ እንዲሁም አካላዊ ርቀትን እንዲጠብቅ የሚመክር ነው።
ጽሑፉ የሰፈረበት መንገድ በመጀመሪያ የተዘጋጀውና ዲዛይን የተደረገው ፈረንሳይ ውስጥ በሚኖር በአንድ ኢአማኒ አልጄሪያዊ ነው ተብሏል።
ኤምና ይህንን ጽሑፍ በፌስቡክ ላይ ያወጣችው የሙስሊሞች የጾም ወቅት በሆነው በረመዳን ጊዜ ሲሆን፤ በወቅቱ ቱኒዚያ በወረርሽኙ ምክንያት በአብዛኛው በእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ነበረች።
ጽሑፉ ከወጣ በኋላ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን አንዳንዶች ኤምና እንድትቀጣ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር። ከቀናት በኋላም በፖሊስ ምርመራ ተደርጎባታል።
ይህንንም ተከትሎ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለስልጣናት ቀደም ሲል የነበሩትን ጨቋኝ ህጎችን በመጠቀም የመናገር ነጻነትን እየተጫኑ ነው በማለት ኤምና ላይ የተመሰረተው ክስ ውድቅ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቦ ነበር።















