ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያዊው የአምቡላንስ ሹፌር ትዝብት የኮሮናቫይረስ ሕሙማንና ሕክምና ላይ
ታሪኩ አትረጋ እባላለሁ። የአምቡላንስ ሹፌር ነኝ። የአምቡላንስ ሹፌር ከሆንኩ አጭር ጊዜው ነው። ገና ሦስት ወራት። ለሹፌርነት ግን አዲስ አይደለሁም። በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር ሹፌር ሆኜ አገልግያለሁ።
ለከተማው አዲስ አምቡላንስ ተሰጠ። አዲስ ሥራዬን በአዲስ መኪና ጀመረኩኝ። መጀመሪያ ወደ ሃገር የሚገቡ ሰዎችን ወደ ኳራንቲን ማዕከላት ማመላለስ ነበር ሥራዬ።
ኢትዮጵያዊያኑ በተለያየ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ ይገባሉ። አድራሻቸው እና ሙቀታቸው ተለክቶ ወደ ለይቶ ማቆያ ይገባሉ። ኮኪት፣ ገንደ ውሃ ወይም ወደ ሌሎች የለይቶ ማቆያ ማዕከላት።
እነዚህ ተጠርጣሪዎች ናቸው። አምቡላንስ ቢሆንም የማሽከረክረው አንድ ላይ የመጡትን እስከ ስድስት ሰባት ሰው ነው የምጭነው።
ወደ ለይቶ ማቆያ የምወስዳቸው በተለያየ ቡድን በመክፈል ነው። ከተለያየ ቦታ የመጡትን ለየብቻ እንለያቸዋለን። ከበረሃ የመጡትን ለብቻ። ከካርቱም የመጡት ለብቻ. . . ንክኪ ይኖራል በሚል የተደረገ ነው።
ለሁለት ሳምንት በለይቶ ማቆያ ከቆዩ በኋላ ናሙና ይወሰድላቸውና ይመረመራሉ።
ከዚያ በኋላ ነው ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች ወደ ህክምና ማዕከል ማመላለስ የጀመርኩት። ብዙ ጊዜ ኮሮና እንዳለባቸው የተረጋገጠባቸውን ሰዎች አመላልሻለሁ። በቁጥር ብዙ ነው። ባህር ዳር 2 ጊዜ ወስጃለሁ። ጎንደር ደግሞ ወደ 12 ወይም 13 ጊዜ ወስጃለሁ።
ከሳምንታት በፊት ዞኑ የተቀበላቸውን አዳዲስ አምቡላንሶች በመጨመር 4 ወይም 5 አምቡላንስ ተመድቦ ነበር ይዘን የምንሄደው።
ከመተማ ጎንደር 190 ኪሜ ይርቃል።
ከጎንደር ባህር ዳር ደግሞ 180 ኪሜ ነው። ስለዚህ ከመተማ ባህር ዳር 370 ኪሜ ይርቃል ማለት ነው። ኮቪድ-19 ባለሙያዎች አንኳን ገና ተጠንቶ ያላለቀ የሚሉት ቫይረስ ነው። ህብረተሰቡም መጀመሪያ ላይ ወዲያው ይገላል የሚል እምነት ነበረው።
በዚህ ወቅት ነው በአካባቢው ሁለት ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የታወቀው። ምልክት አልነበረባቸውም። አንዱ ሱዳን በረሃ የዕለት ሠራተኛ ሌላው ደግሞ የካርቱም ነዋሪ።
እነዚህን ነው ከጤና ባለሙያ እና ከጸጥታ ሃይል ጋር በመሆን ወደ ጤና ተቋማት መጀመሪያ የወሰድኳቸው እኔ ነኝ።
ከካርቱም የመጣው ግለሰብ '[ቫይረሱ] ቢኖርብኝም ማገገም እችላለሁ። ግን የለብኝም። ምንም ዓይነት ምልከት ሳይኖረኝ እንዴት አለብህ ትሉኛላችሁ? ይሄ ስህተት ነው። ወደ ቤተሰቦቼ እንዳልሄድ እያደረገቻሁኝ ነው' በሚል ቅሬታ አሰምቷል።
ወደ አምቡላንሱ እንዲገባም የጤና ባለሙያ ምክር አስፈለጎ ነበር።
ጥንቃቄን በተመለከተ አምቡላንሶቹ ከኋላ ሙሉ ዝግ ናቸው። አቀማመጣቸውም የተወሰነ [ከእኛ] ርቀት አለው።
ቫይረሱ አለባችሁ ሲባሉ የሚረብሹ ስላሉ። የግንዛቤ ማስጨበጫ እንሰጣቸዋለን።
[ቫይረሱ] አለባችሁ ሲባሉ 'የለብንም ስህተት ነው። ውሸት ነው' ብለው የሚረብሹ፤ መስኮት ለመክፈትም ሆነ ለመስበርም የሚታገል አለ። 'አልሄድም' ብሎ የሚገላገልም አለ።
እኛ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እና የእጅ ጓንት እንጠቀማለን። ባህር ዳር የሚገኘው የህክምና ማዕከል ስንደርስ ጸረ-ተዋሲያን ርጭት ያደርጋሉ። ጎንደር ላይ ግን ለማድረግ ራሱ ዝግጁ ሆነው አይጠብቁም። ባህር ዳር ይዤ ስሄድ በአግባቡ መድኃኒት ይረጫል። እኔ ራሱ መሬት ላይ አልወርድም። ጎንደር ግን 'ተቀበሉን አንቀበልም' በሚል አንደ ሰዓትም ብዙ ጊዜ 30 ደቂቃ እቆማለሁ።
ሕሙማንና የተለየየ ባህሪያቸው
አንዳንዴ ኬዝ [ቫይረሱ ያለበት ሰው] ጭነን ስንቆም 'በግድ ነው ያመጣችሁን። እነሱ ራሱ አንፈልጋችሁም እያሉን ነው ይሄን ያህል ያቆሙን። የት ነው የምትወስዱን?' እያሉ ብዙ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት አሰጣ አገባዎች አሉ።
የመተማ ልጅ ስለሆንኩ የአካባቢውን ህብረተሰብ ባህሪ ስለምረዳ ሳናግራቸው ይረዳሉ። ቁጣ ምናምን ከቀላቀልክ አይሆንም።
በኋላ በኋላ ከኳራንቲን ቫይረሱ አለባችሁ ተብለው ወደ ህክምና ማዕከላት የሚሄዱ ሰዎች [የሚሄዱበትን ማዕከል] ማማረጥ ጀመሩ።
በህክምና ማዕከላት እና በለይቶ ማቆያ ያሉት ስልክ ተደዋውለው መረጃ ይለዋወጣሉ። [ባህር ዳር የተሻለ ነው ስለሚሏቸው] ቫይረሱ ተገኘባችሁ ሲባሉ 'ባህር ዳር ከሆነ ውሰዱን ጎንደር ግን አንሄድም' የሚል ባህሪ እያመጡ ነው።
የመጀመሪያ ሁለት ኬዝ ይዤ ስሄድ አንዱ የሲጋራ ሱስ አለበት። ለካ ሲጋራ ይዞ ነበር። ልክ ጎንደር እንደገባን 'ሲጋራ ልለኩስ ነው' አለ። ሲገባ ፍተሻ ስላልተደረገበት ሲጋራ ይዟል።
'ልለኩስ?' ሲል ለሁላችንም መጥፎ ነው እንዳትለኩስ አልነው። ቆይቶ 'እሺ በቃ ሽንቴን ልሸና ነው በቃ አውርዱኝ' አለ።
በወቅቱ ቫይረሱ አዲስ እና በእኛም አይታወቅም ነበር። አንዴ ጉዞ ከጀመራችሁ በኋላ ባህር ዳር ነው የምትቆሙት ተብለናል። መንገድ ላይ ማውረድ አንችልም ማለት ነው። እንደተባለው አደረግን።
ባህር ዳር ማታ አካባቢ ነበር የገባነው። ወደ 4 ሰዓት ገደማ ነበር የገባነው። ልክ ከተማ ከገባን በኋላ 'አልቻልኩም ከፈለጋችሁ አውርዳችሁ ግደሉኝ እንጂ' ብሎ ሲጋራውን አውጥቶ ለኮሰ።
አብሮኝ ጋቢና ያለው የህክምና ባለሙያ ነው። የጸጥታ አባሉ በሌላ መኪና ነበር። አይዞህ እያልን እያበረታታን ሲጋራውን አስጥለን ወደ ህክምና ማዕከል አስገባነው።
አንድ ጊዜ ደግሞ ስምንት ኬዝ ተገኘ። ለህክምና ጎንደር ነበር የሚሄዱት።
ከህክምና ማዕከሎች ጋር መተዋወቅ ሲመጣ እየደወሉ አምጣ ሲሉኝ በቀጥታ ይዤ እሄዳለሁ።
በወቅቱ ከሱዳን ወደ ሃገር ውስጥ በጫካ በኩል አዲስ የሚመጡትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እና የሙቀት ልኬታ ስላለ የጸጥታ መዋቅሩም ሥራ በዝቶበት ነበር።
ስምንቱን ይዤ እንድሄድ የጸጥታ አካል አብሮኝ መሳፈር ያስፈልግ ነበር።
ከጤና ባለሙያ ወደ ህክምና ማዕከል የማስገባበት ወረቀት ተሰጥቶኛል። የቀረው የጸጥታ መዋቅር አባሉ ከእኔ ጋር ጋቢና ሆኖ ማድረስ ነው።
ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች አምቡላንሱ ውስጥ ጫንኩኝ። አባሉ ወጥቻለሁ ቢለንም ስንጠብቀው የለም። ዝም ብዬ ነዳሁት።
ግማሽ መንገድ ከደረስን በኋላ 'ሽንታችን ስለመጣ አውርደን' አሉ። 'እንዴት አደርጋለሁ?' የሚል ጭንቀት ያዘኝ።
'ችግር የለም ግን ከተማ ላይ ማቆም አይቻልም። ጫካም ለእናንተ [ደህንነት] ጥሩ ስላልሆነ ከተማ ላይ አንድ የጤና ማዕከል ገብተን ሸንታችሁ ተጣጥባችሁ ትሄዳላችሁ' አልኳቸው። አሁን አሁን እያልኩ እያዋራሁ እያሳሳቅኩኝ ጎንደር ከተማ ገባን።
መንገድ ላይ እንደፈለጉ መሆን ይፈልጋሉ፤ ሲጋራ ማጨስ ሽንታቸውን በተለያየ ሰዓት መሽናት ይፈልጋሉ። ከዚያ ውጭ ብዙም ችግር የለባቸውም።
አብዛኛዎቹ በሚዲያ የሚተላለፈውን ይሰማሉ። 'ለምን አንድ በአንድ አትወስዱንም?' ሲሉ ይጠይቃሉ። 'መቼም በሃገሪቱ ሁኔታ ለስምንት ሰው ስምንት አምቡላንስ አይመደብም' እንላቸዋለን። 'አንድ ላይ የተገኛችሁ ስለሆናችሁ አንድ ላይ ትሄዳላችሁ። አንድ ሰው ከተገኘበት ለብቻው ነው የሚሄደው ነው' የምላቸው።
[ለይቶ ማቆያ ያሉት] ተደጋጋሚ ጊዜ ቫይረሱ ያለባቸውን እንደማመላልስ ሰለሚያውቁ ናሙና ሰጥተው ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ወደ ህክምና ማዕከል ለመውሰድ ስጭናቸው 'ታሬ ታሬ የት ነው የምትወስደን? ባህር ዳር ነው ጎንደር?' ይሉኛል። "እናንተ እንደምርጫችሁ ባህር ዳር ያለ ባህር ዳር፤ ጎንደር ያለ ጎንደር እላለሁ።" ምክንያቱም እንዲህ ካልካቸው ነው ተስማምተህ ልትነዳ የምትችለው። እንዲህ ካላልካቸው አትስማማም።
እኛ ጎንደር እና ባህር ዳር የህክምና ማዕከላት ይዘን እንሄድ ስለነበር ሁሌም ያጠናሉ። 'የተሻለ ምግብ የሚያቀርቡልን የት ነው ጎንደር ነው ወይስ ባህር ዳር ነው?' ይላሉ። የምትፈልጉት ማዕከል አስገባችኋለሁ እላለሁ።
ያው እኔ የጤና ባለሙያው በሚለኝ ነው የምሄደው። ጎንደር ካለኝ ጎንደር እሄዳለሁ። ግን የምትፈልጉት ቦታ እወስዳችኋለሁ ስላቸው 'ባህር ዳር፣ ባህር ዳር' ይሉኛል።
ኮቪድ-19 እና የሕሙማን ግንዛቤ
በኮቪድ ጉዳይ ጥቂቶች ናቸው በሽታው ስለመኖሩን የሚያውቁት። ከዚያ ውጭ ግን እንደ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ብራዚል፣ ስፔን እና ጣሊያን ሞት ካላየ የማያምን ህብረተሰብ ነው ያለው እኛ አካባቢ። እኛ አካባቢ ውሸት ነው የተባለበት ጊዜም አለ። ምክንያቱም 'አላሳለኝ፣ ሙቀት አልተሰማኝ፣ ሙቀቴ አልጨመረ። ጤነኛ ሰው ነኝ። እንዴት አለብህ ትሉኛላችሁ?' ይላሉ። ብዙዎች አለባችሁ የሚባሉትም አልተዋጠላቸውም። በትክክል ተገኝቶብኛል ብሎ ራሱን ያሳመነ አካል የለም።
ቫይረሱ ያለባቸውን እና ተጠርጣሪዎችን ሳመላልስ ሙሉ ከተማው ይጠቋቆምብኝ ነበር። ምክንያቱም ኮኪትም ገንደ ውሃ [ከተሞች] ላይ ሳልፍ በጣም እሯሯጥ ነበር።
'ኮቪድ የሚያመላለስው ማነው?' ሲባል 'የመተማው ሹፌር- የመተማው ሹፌር ታሪኩ የሚባል ነው' ይላሉ።
እኔ ራሱ ቫይረሱ ያለባቸውን ባህር ዳር ወስጄ ስመለስ ሌላ ቦታ ወርጄ ሻይ መጠጣት ተሳቀቅኩኝ። ሻይ መጠጣት እፈልጋለሁ ግን ተሳቀቅኩኝ። ማህበረሰቡ 'ከኮቪድ ጋር በተያያዘ የሚሠራ ሰው ራሱን አግልሎ ማግለያ ውስጥ መቀመጥ አለበት ነው' የሚለው።
እኔ ሹፌር ሆኜ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ስሠራ ጀምሮ ከቤተሰብ ጋር ከሚስቴ ጋር መቀላቀል የለበኝም። ተመቻችቶ ለብቻዬ ኳራንቲን ሆኜ ከማህበረሰቡ፣ ከእናቴ እና ከባለቤቴ ጋር መቀላቀል አልነበረብኝም።
አድርሼ ስመለስ ጓደኞቼ አትቀላቀልም በሚል ከአንገት በላይ ነበር ሠላም የሚሉኝ። አሁን ግን ለውጥ አለው። 'ችግር የለም ሰላም በለን' የሚልም አለ። አሁን ተለምዷል። መጀመሪያ ግን 'መተማ ላይ [ቫይረሱ] ከገባ እሱ ነው የሚያስገባብን' በሚል እኔ ላይ ያነጣጠረ ጥሩ ያልሆነ ሁኔታ ነው የነበረው።
ከጊዜ ወደ ጊዜ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ስለጨመረ ከአምቡላንስ አቅም በላይ ሆነ። ጎንደር ዩኒቨርሰቲ አውቶብስ ስለሰጠን እሱን እየተጠቀምን ነው። አንዴ ኬዝ ሲመጣ ከ20 በላይ ስለሚሆን አምቡላንስ ስለማይበቃ ዩኒቨርሲቲው በሰጠን አውቶብስ እየተመላላሱ ነው።
አሁን ከጸጥታ እና ህክምና ባለሙያዎች ጋር በመሆን በጫካ በኩል ወደ ማህበረሰቡ የገቡ ስለሚኖሩ እነሱን እየሄድኩ ከጸጥታ መዋቅር ጋር ወደ ገንደ ውሃ እና መተማ ኳራንቲን ነው የማስገባው። ቫይረሱ ያለባቸውን ወደ ህክምና ማዕከል አላመላልስም።
በመተማ ድንበር የሚመጡ የበረሃ ሠራተኞች የተለያየ የሱስ ሁኔታዎች ያለባቸው አሉ። ሲጋራ፣ ሺሻም ጫትም ሱስ ያለባቸው አሉ። ለይቶ ማቆያ ከገቡ በኋላ ሁሉን ያጣሉ።
ለይቶ ማቆያ ከገቡ በኋላ 'የምንበላው አይመቸንም' በማለት የሚጠፉ አሉ። ለይቶ ማቆያ ከገቡ በኋላ ሁለት ሳምንት ሞልቷቸውም 12 ወይም 13 ቀን የቆየ ሌላ ሰው ናሙናው ሲወሰድ እኛ 14 ቀን ሞልቶን ለምን አይወሰድልንም በሚል 14 ወይም 15 ቀን ሞልቷቸዋው ለሊት ላይ ከፀጥታ መዋቅሩ በመሸሸግ ከተለያዩ ማዕከላት ያመልጣሉ።
በህዝብ ክትትል እና ጥቆማ ይያዛሉ። መጀመሪያ ከቢቢሲ ሲደወልልኝ '14 ቀን ሞልቶኛል። ናሙና መወሰድ ነበረበት። ካልተወሰደ ለምን እቀመጣለሁ?' በማለት ወደ መንደር 7 ከተማ የጠፋ ግለሰብ ለመያዝ እያቀናሁ ነበር። እንደጠፋ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ መንደር ሰባት ላይ ተያዘ። ከቦታው ድረስ ሄጄ አምጥተነው ናሙና እንዲሰጥ አድርገናል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ ምንም ዓይነት ስሜት የለኝም። መሥራት ከጀመርኩ ራሴንም አሞኝ አያውቅም። ሙሉ ጤነኛ ነኝ። ግን ስጋት ነበረኝ። ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች ሳይ ምንም ምልክት የለባቸውም። በወቅቱ ሳመላልሳቸው ንጹህ ሰዎች ናቸው። አንዱን አውርጄ ሌላ ለመጫን መኪናውን ጸረ-ተዋህሲያን የሚረጨው ጠፍቶ ለመርጨት የምገደደበት ጊዜ አለ። ሥራው የህሊና ሥራ ስለሆነ ራሴ በጸረ-ተህዋሲያን መኪናውን አጸዳለሁ። አጣዳፊ ሲሆን የእጅ ጓንትም ሲያልቀብኝ አልኮል ያለው ማጽጃ (ሳንታይዘር) እጄን ረጭቼ በር እከፍት ነበር። ራሴን እጠራጠር ነበር። ከሳምንት በፊት ተመረመርኩኝ። ነጻ ሆኜ ተገኘሁ። ከዚህ በኋላ ግን በደንብ እንደምጠነቀቅ ነው የተማርኩበት።
ኢትዮጵያ ውስጥ ኮቪድ አስጊ ከሆነባቸው ቦታዎች አንዱ ምዕራብ ጎንደር ነው። ከሱዳኖች ጋር ፊት ለፊት እየተያየን እየተጨባበጥን ነው የምንኖረው። የ10 ሜትር ልዩነት ናት።
ዋናው ቦታ ደግሞ መተማ ዮሃንስ ላይ ነው። ኬላውን ሲከፍቱ ምናምን እንተያያለን። እንደሃገር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ አይደለም። ብዙ በሮች እና ፍሰት ያለበት ቦታ ነው።
የሱዳን ኬዝ ሲጨምር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው ፍልሰት ይጨመራል። በረሃ ውስጥ ከሚሠሩት በተጨማሪ ከተማ ላይ የሚኖሩም እየመጡ ነው።
መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት። ባለው የበጀት ምክንያት ጸረ-ተዋህሲያን በአግባቡ አያመጡልንም። የእጅ ጓንት እና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አይመጣልንም። በነበረው ነው የምንጠቀመው። ከኮሮና ኬዝ በኋላ የገባልን ነገር የለም። ኮታው እየጨመረ ነው። ግን የደረሰ ነገር የለም። የጸጥታ መዋቅሩም ንክኪ አለው ማለት ይቻላል። እየተጋለጠ ነው። [ተጠርጣሪዎችም ሆኑ ቫይረሱ ያለባቸው] አንሄድም ሲሉ ገፍተው ያስገቧቸዋል። ለምርመራ ጎንደር እና ባህር ዳር መኬድ የለበትም። ለምን ገንደ ውሃ አይሆንም። በሽታው እንደ ሃገር እየተስፋፋ ነው። እየተከላከለን አይደለም። ብቻ ያስቡበት።