"እንደ ቆሻሻ ነው አውጥተው የወረወሩን" ኢትዮጵያውያኑ በሊባኖስ

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እየተባባሰ የመጣውን የሊባኖስ ምጣኔ ሃብት ማሽቆልቆል የኢትዮጵያውያኑን የቤት ሠራተኞችንም ኑሮ አክፍቶባቸዋል።

በርካታ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሊባኖሳውያንም ለቤት ሠራተኞቻቸው መክፈል አንችልም በሚልም እያባረሩ ይገኛሉ።

በዚህ ሳምንትም 100 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች በመዲናዋ ቤይሩት በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ በር ላይ አሰሪዎቻቸው አምጥተው ትተዋቸው ሄደዋል።

ሦስት ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች በአንድ ሰዓት ውስጥ በቆንስላው በር ላይ አሰሪዎቻቸው ትተዋቸው ሲሄዱ የቢቢሲው ጋዜጠኛ ማርቲን ፔሺየንስ ለመታዘብ ችሏል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች ሲብረከረኩ፣ ሲያለቅሱ እንዲሁም የሚሄዱበት የሚጠለሉበት ጥፍት ብሏቸው ታይተዋል። አንዳንዶቹም ግራ በመጋባት ሲንቀጠቀጡና ሲጮኹ፣ አንደኛው አሰሪም ከኋላ ያነገተውን ሽጉጥ ሲመዝም ታይቷል።

በቆንስላው በር በቀዝቃዛው አስፓልት በስስ ምንጣፍ ላይ ተኝተው የሚያሳየውም ምስልም የሚረብሽ ነው። በበሩ ላይ ተበትነው የሚታዩት ኢትዮጵያውንም እርስ በርሳቸው ሲፅናኑ፣ እንዲሁም ተደጋግፈው ይታያሉ።

የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝን ተከትሎ በደረሰው ጫና ምክንያት አሰሪዎቻቸው ደመወዝ ሳይከፍሉ ኢትዮጵያውያኑን አባረዋቸዋል። በርካታ ሠራተኞችም የሚላስ የሚቀመስ እንዳጡም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት ብዙዎች የእለት ጉርሳቸውን በቤት ሠራተኝነት በሚያገኟት ደመወዝም መሸፈን ይችሉ ነበር። ከእነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያዊቷ ሎሚ አንደኛዋ ናት። የወራት ደመወዟን በአሰሪዋ ያልተከፈላት ሎሚ ሁኔታው ከድጡ ወደማጡ ሆኖባታል።

"ወደአገራችን እባካችሁ መልሱን፤ አሰሪዎቻችን ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ አላገኙንም ፤ እኛ ቆሻሻ አይደለንም እንደዚህ እንደ ቆሻሻ የሚወረውሩን" ብላለች።

ትዕግስት መስፍን የምትባል በጎ ፈቃደኛ በቦታው ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እርዳታ እያደረገች ሲሆን፤ ሁሉም ወደ አገራችን መልሱን የሚል ተማፅኖቻውን እያሰሙ እንደሆነና ወረርሽኙን ተከትሎ የአየር ማረፊያዎች ከመዘጋታች አንፃር ጊዜያዊ መፍትሄ ሊፈለግላቸው ይገባልም ብላለች።

"በረራ እስኪጀመር ድረስ ቤትውስጥ እንዲቆዩና የሚሰሩበትም መንገድ እንዲመቻችላቸው" በቆንስላው ውስጥም ባሉ መጠለያዎች ውስጥ በጊዜያዊነት ማረፊያ እንዲሰጣቸው ጠይቃለች።

"ለምን ኤምባሲውን ከፍተው ማደሪያ አይሰጧቸውም? ስህተት ነው" ትላለች ትዕግስት።

የሠራተኛ መብት ተከራካሪዎች እንደሚሉት የቤት ሠራተኞቹ ሁኔታ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ካፋላ በተባለው አወዛጋቢና አግላይ ሥርዓትም መብታቸው ተገቷል።

ፋራህ ሳልካ የተባለችው የፀረ- ዘረኝነት እንቅስቃሴ ዳይሬክተር እንደምትለውም በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሠራተኞችን ይህ ሥርዓት ከሊባኖስ የሠራተኛ ሕግ ሆን ብሎ ያገላቸዋል ትላለች።

ለምሳሌ ማግኘት የሚገባቸው ክፍያ፣ ዓመታዊ ፈቃድ፣ የሳምንት እረፍት እንዲሁም በቀን ውስጥ ምን ያህል ሰዓት መስራት አለባቸው የሚለው በሙሉ እንዳይመለከታቸው ተደርጓል።

ከዚህም በተጨማሪ በአሰሪዎቻቸው በደል ቢደርስባቸው መውጣት የሚችሉበት እንዲሁም አቤቱታ ማቅረብ እንዳይችሉ ተደርገዋል። "ይሄ ሥርዓት ማለት በቤታችን ውስጥ ያለ የዘመኑ ባርነት ነው" ብላለች።

አንዳንዶች አገሪቱ ውስጥ ባሉ የእርዳታ ድርጅት መጠለያ የተሰጣቸው ሲሆን መንግሥትም የቻልኩትን እያደረግኩ ነው ብሏል።

ማርሊን አታላህ የሊባኖስ የሠራተኞች ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጄኔራል እንደተናገሩት ከኢትዮጵያ ቆንስላ ጋር አብረን እየሰራን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያኑ የቤት ሠራተኞች በሆቴል ውስጥ ለሁለት ቀናት ያህል እንዳሳደሯቸውና ወደ መጠለያዎችም ወስደናቸዋል ብለዋል።

ለቤት ሠራተኞቹ ደመወዝ ባለመከፈልም ሆነ በመባረራቸው የተከሰሰ አሰሪ የለም፤ ነገር ግን ምርመራዎች እንደተጀመሩ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቆንስላ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።