ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ያቀጣጠለው የቻይናና የአሜሪካ ፉክክር በአፍሪካ
ዘግየት ብሎ የኮሮናቫይረስ በተከሰተባት አፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ አሜሪካና ቻይናም ለአህጉሪቱ ከፍተኛ ድጋፍ በመስጠት እኔ እበልጣለሁ በሚል እሰጣገባና እሽቅድምድሞሽ ተጠምደዋል።
ሁለቱ አገራት እያደረጉት ያለው ፉክክር በአፍሪካ የቫይረሱን ስርጭት ከመቆጣጠር በዘለለ ኃያልነታቸውን የማስፈን ተግባር እንደሆነ የቢቢሲ አፍሪካ ዘጋቢው አንድሪው ሃርዲንግ ያትታል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ ከሰሞኑ "በአፍሪካ ውስጥ ኮቪድ-19ን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለውን ትግል የሚደግፍ ከአሜሪካ በላይ አገር ከየትም አይመጣም" ያሉ ሲሆን አክለውም "ለዓለም አቀፉ የጤና ሥርዓት አሜሪካ እንደምታደርገው ድጋፍ የትኛውም አገር አድርጎ አያውቅም፤ መቼም አይደረግም" ብለዋል።
ማይክ ፖምፔዮ ይሄንን ያሉት በአፍሪካ ውስጥ ካሉ ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ነው። የቢቢሲው አንድሪው ሃርዲንግም 'አንዱ እኔ ነበርኩ" ይላል።
ባለፈው ወርም እንዲሁ በትራምፕ አስተዳደደር የተለመደውን "ማንኛውም አገር ከእኛ በበለጠ አይሰራም" የሚለውን ንግግር ከአሜሪካ ባለስልጣናት የተሰማ ሲሆን፤ እንዲህ አይነት ተደጋጋሚ ንግግርም የሚሰማው አገሪቱ ለዓለም ጤና ድርጅት የምታደርገውን ድጋፍ ከማቋረጧ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ትችቶችን ፀጥ ለማሰኘት ነው።
በተለይም አሜሪካ ለድርጅቱ ታደርገው የነበረውን ድጋፍ ይህ ዓለም አቀፍ ቀውስ ጣራ በነካበት ወቅት ከማቋረጧ ጋር ተያይዞ ብዙዎች ወቀሳቸውን አሰምተዋል። አሜሪካም ከዚህ ለማምለጥ ጥረት እያደረገች ነው።
ማይክ ፖምፔዮ አሜሪካ ለአፍሪካ አድርጋዋለች ብለው ከሚኮሩበት የገንዘብ እርዳታ መጠን በቅርቡ የተለገሰው 170 ሚሊዮን ዶላር ነው። ነገር ግን ይህ የገንዘብ መጠን ከቻይና እንደ አገር ከተሰጠው ቀርቶ ቻይናዊው ቢሊየነር ጃክማ ከሰጠው ጋር ሲወዳደር ያንሳል።
ከሰሞኑ የአሜሪካና የቻይና ባለስልጣናት አህጉሪቷ ጋር በተያያዘ የሚያደርጓቸውን ንግግሮችን ለታዘበ አፍሪካ ለሁለቱ ኃያላት አገራት አዲሱ የቀዝቃዛ ጦርነት ሜዳ መሆኗን ለመረዳት አይቸገግርም።
ከዚህ ቀደምም ሁለቱ አገራት የነበራቸው የቃላት ጦርነት በኮቪድ-19 ቀውስ የተባባሰ ሲሆን አህጉሪቷንም ማዕከል በማድረግ ወደ ውክልና ጦርነት እያመሩ ይመስላሉ።
"የከሸፈው መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ"
በቅርቡ በቻይና መንግሥት ቁጥጥር ስር ያለው ግሎባል ታይምስ ይዞት በወጣው ፅሁፍ አገሪቱ እያራመደች ያለችው የፖለቲካ ሥርዓት የኮቪድ-19ን ስርጭት ለመግታት እንዴት እንደጠቀማት ያትታል።
በመቀጠልም የከሸፈው የምዕራባውያን መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ በአፍሪካ አገራት ላይ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ተበላላጭነት፣ የብሔርና የሐይማኖት መከፋፈል፣ ግጭት እንዲሁም የህይወት መጥፋትና የንብረት መውድም ማስከተሉን አስፍሯል።
እናም አፍሪካውያን ከዚህ ከከሸፈ ሙከራ ራሳቸውን ገሸሽ በማድረግ የቻይናን የአንድ ፓርቲ መንገድ ሊከተሉ እንደሚገባም ምክር ለግሷል።
በቻይና መንግሥት ቁጥጥር ስር ያለ ዕለታዊ የቻይና ጋዜጣም እንዲሁ ቻይና በአህጉሪቷ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ እያፈሰሰችው ያለችውን መዋዕለ ንዋይና ኢንቨስትመንት አፍሪካን ከታሪካዊ ጭቆና እንዲሁም አሁን ካለችበት መበዝበዝ ያድናታል ብሏል።
"አፍሪካ ለምዕተ ዓመታት በባርነት ቀንበር፣ ቅኝ ግዛት፣ እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አሁን ደግሞ በኮሮናቫይረስ ቀውስ ውስጥ ገብታለች። የቻይና የመዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ አላማም አህጉሪቱ ከዚህ አዙሪት እንድትወጣና እንድታገግም ነው" በሚልም አስፍሯል።
የቻይና መንግሥት ለአፍሪካ እያደረገ ያለውን ኢንቨስትመንት ማንቆለጳጰስ ለማይክ ፖምፔዮ አልተዋጠላቸውም። የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ በአፍሪካውያን ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍና ለረዥም ዘመናት የሚቆይ የእዳ ጫና እየከመረባቸው ነው ሲሉ ወርፈዋል።
በቅርብ ቀናትም የቻይናና አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ አንድ ውይይትም ተደርጎ ነበር። የውይይቱ አስተናባሪ ሁለቱ አገራት በአህጉሪቱ ላይ የሚያደርጉትን እሽቅድምድም "መርዛማ" ብለውታል።
በወቅቱም አንድ የቻይና ፐሮፌሰር ኮሮናቫይረስ ለአፍሪካውያን ጋዜጠኞች የቻይናን የሚዲያ እሴቶችና ጥሩ ተሞክሮ እንዲያደንቁ አድርጓቸዋል ብለዋል።
"የምዕራባውያን ሚዲያ በጨለምተኛ ዜና የተሞላ ነው፤ ሁሌም አሉታዊ ነው" ያሉት ፕሮፌሰር ዛንግ ያንኪዩ በእንደዚህ አይነት ቀውስ ወቅት ግን ተስፋን የሚፈነጥቁ ታሪኮችን ሰዎች ማንበብ ይፈልጋሉ ብለዋል።
በሌላ መንገድ አፍሪካውያን የቻይና የሚዲያ ሞዴል የሆነውን 'ገንቢ ጋዜጠኝነት'ን (constructive journalism) ይፈልጋሉ ብለዋል። በቅርቡም ፕሮፌሰሯ በኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ዘንድ ለገንቢ ጋዜጠኝነት ያላቸውን ጉጉትና ፍላጎት መታዘባቸውን አስረድተዋል።
ነገር ግን ጥያቄው የአፍሪካ ጋዜጠኝነት እንዲህ በቀላሉ ተፅእኖ ውስጥ የሚወድቅ ነው?
በንግግራቸው አወዛጋቢ የሚባሉት ትራምፕ ለኮሮናቫይረስ መድኃኒቱ ፀረ-ተህዋሲ (ዲስኢንፌክታንት መጠቀም) እንዲሁም የፀሐይ ጨረር ፈውስ ነው ማለታቸው በአፍሪካውያን ዘንድ ያላቸውን ስም የበለጠ አላጠለሸውም ወይ ተብለው የተጠየቁት ማይክ ፖምፔዮ በቀጥታ አልመለሱም።
ነገር ግን ትራምፕ የሚያደርጓቸው ንግግሮችን ብዙ ሰው እንደማይረዳው እንዲሁም በመንግሥት ቁጥጥር ስር ባሉ ሚዲያዎች ሆን ተብሎ ሌላ ትርጉም ይሰጣቸዋል ብለዋል።
ከማይክ ፖምፔዮ ጋር የነበረው ቆይታ ለበርካታ ጋዜጠኞች እንግዳ የሆነ ክስተት የተስተናገደበት ነበር።
ለአስርት ዓመታት አሜሪካ በአፍሪካ የምትከተለው ዲፕሎማሲ በተወሰነ ደረጃ አምባገነን መንግሥታትን የሚቃወም፣ ከሳንሱር ነፃና ገለልተኛ ጋዜጠኝነትን መሰረት ያደረገ ነበር።
ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሚተቿቸውን የአገራቸውን ጋዜጠኞች "ሐሰተኛ" "የሕዝብ ጠላት" በማለት መወንጀልና ማዋረድ የየዕለት ሥራቸው ሆኗል።
ምናልባትም የአሜሪካና የቻይና ገንቢ የጋዜጠኝነት ሃሳብ መንግሥትን አለመተቸት ከሆነ እሳቤያቸው ተቀራርቧል ማለት ይቻላል።
በቀድሞው የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር ወቅት አሜሪካ ፔፕፋር በተባለው ፕሮግራም ለኤድስ የሚውል እርዳታን ለአፍሪካ የጤና ሥርዓት ተለግሷል።
አሜሪካ ካላት የውስጥ ትግልና መከፋፈል ጋር ተያይዞ በአሁኑ ሰዓት ቻይና የኮሮናቫይረስን ሽፋን በማድረግ በአፍሪካ ላይ ፖለቲካዊ አጀንዳዋን ለማስረፅና አሻራም ለማሳረፍ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
የአፍሪካ አገራትም ሆነ ጋዜጠኞች ባለው የልዕለ ኃያላን ጉልበት ተጽእኖ ተንበርክከው የሚያሸረግዱ ላይሆኑ ይችሉ ይሆናል።
ነገር ግን በርካታ አገራትም ባለባቸው ከፍተኛ የቻይና የብድር ጫና እንዲሁም የኮሮናቫይረስ ባስከተለው የኢኮኖሚ ድቀት የተነሳ "የከሸፈ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን" ገሸሽ በማድረግ የቻይናን የፖለቲካ ሥርአት ይቀበሉ ይሆን? የምናየው ይሆናል።