ኮሮናቫይረስ፡ ለመሆኑ ጽኑ ሕሙማን ክፍል ምንድን ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ትናንት አመሻሽ ላይ ሕመማቸው ስለበረታ ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል መግባታቸው ተሰምቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት እንዳለው በሐኪሞቻቸው ምክርና ለቅድመ ጥንቃቄ በሚል የተሻለ የቅርብ ክትትል ወደሚያገኙበት ክፍል መግባታቸውን ገልጿል።

ለመሆኑ ጽኑ ሕሙማን ክፍል ምንድን ነው?

የሕክምና ባለሙያዎች የጽኑ ሕሙማንን ክፍል በእንግሊዘኛ ምህጻረ ቃሉ አይሲዩ (ICU) ሲሉ ይጠሩታል። ይህ ክፍል በጠና የታመሙ ሕሙማን በሐኪሞቻቸው የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው የሚታከሙበት ክፍል ነው።

እነዚህ ክፍሎች በተቻለ መጠን በአስፈላጊ የሕክምና ቁሳቁሶች የተደራጁ መሆን ይኖርባቸዋል።

አንድ ታካሚ በተለያየ ምክንያት ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል ገብቶ መታከም ሊያስፈልገው ይችላል።

አንዳንድ ሕሙማን ከቀዶ ሕክምና በኋላ እስኪያገግሙ ድረስ በዚህ ክፍል እንዲቆዩ ሲደረግ፣ አንዳንዶች ደግሞ ከከባድ የመኪና ወይንም ሌላ አደጋ በኋላ በዚህ ክፍል የሕክምና ክትትልና ድጋፍ ይደረግላቸዋል።

ኮሮናቫይረስ የሚያጠቃው የመተንፈሻ አካላትን በመሆኑ ወደ ጽኑ ሕክምና ክፍል የሚገባ ታማሚ የመተንፈስ ችግር አጋጥሞት ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን ይህ ማለት የመተንፈሻ ማሽን ሊገጠምለት ይችላል ወይንም በማሽን ታግዞ መተንፈስ ያስፈልገዋል ማለት እንዳልሆነ ባለሙያዎች ያብራራሉ።

በርግጥ በጽኑ ሕሙማን ክፍል ያሉ ታካሚዎች የተለያዩ መሳሪያዎች ተገጥመውላቸው የመተንፈስ ችግራቸው እንዲቃለል ሊደረግ እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ከእነዚህም መካከል CPAP ሲሆን ታካሚው በሚደረግለት ጭምብል በኩል ኦክስጅን እንዲያገኝ የሚረዳው መሳሪያ ነው።

በዚህ የሕሙማን ክፍል የሚቆዩ ታካሚዎች የሚያስፈልጋቸው መድኃኒት እየተሰጣቸው መሻሻል እስኪያሳዩ ድረስ ክትትል እየተደረገላቸው ይቆያሉ።

ታካሚው መሻሻል እንዳሳየ ግን ወደ ተኝቶ ታካሚዎች ወይንም ሌላ ክፍል የሚዛወር እና የክፍሉን አልጋ ለሌሎች በአፋጣኝ የዚህ ክፍል እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሕሙማን የሚለቁ ይሆናል።

አንዳንድ ሕሙማን ለተወሰኑ ቀናት በዚህ ክፍል መቆየት ሲያስፈልጋቸው፣ አንዳንዶች ግን ለሳምንታትና ለወራት ቆይተው መታከም ይኖርባቸዋል።