ሰሜን ኮሪያ ኮሮና የለብኝም ትላለች፤ እንዴት እንመናት?

አንድም ሰው በኮሮና አልተያዘብኝም ትላለች ሰሜን ኮሪያ። ጥብቅ እርምጃ ስለምወስድና ድንበሮቼን ከርችሜ ነው ይህን ውጤት ያመጣሁት ስትል ታብራራለች።

ይህንን ለመቀበል እቸገራለሁ ይላሉ በደቡብ ኮሪያ የአሜሪካ ጦር ኮማንደር።

ሌላ ሰሜን ኮሪያዊ ኤክስፐርት በበኩላቸው የተያዘ ሰው አይኖርም ባይባልም በብዙ ቁጥር ላይሆን ይችላል ሲሉ ይገምታሉ።

በዚህ ወቅት በመላው ዓለም የተያዦች ቁጥር 1 ሚሊዮን አልፏል።

ከ53ሺ በላይ ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል። ሰሜን ኮሪያ ግን በዚህ ቁጥር ውስጥ የኔ ዜጋ አንድም የለበትም ትላለች።

ፓክ ዮንግ ሱ የተባሉ የሰሜን ኮሪያ የጤና ባለሥልጣን አንድም ሰው እንዳልተያዘ በድጋሚ አረጋግጠው ይህም የሆነው ድንበሮቻችንን ስለዘጋን፣ ወደ አገራችን የገባውን ለይተን ስላስቀመጥንና ሰው የሚበዛባቸው አካባቢዎችን በሙሉ ጸረ ቫይረስ መድኃኒት በመርጨታችን ነው ይላሉ።

ይህ ግን ምን ያህል እውነት ነው?

የአሜሪካ የጦር ጄኔራል ሮበርት አብራምስ ሰሜን ኮሪያ የምትለው ነገር ቅጥፈት ነው ይላሉ። አርሳቸው በጎረቤት ደቡብ ኮሪያ የሚገኘው የአሜሪካ ጦር አዛዥ ናቸው።

‹‹እኛ ባለን መረጃ ይህ እውነት እንዳልሆነ አሳምረን እናውቃለን›› ይላሉ ጄኔራሉ።

ሆኖም ጄኔራሉ የተያዙት ሰሜን ኮሪያዊያን ምን ያህል እንደሆኑና የት እንደሚገኙ መናገር አልቻሉም።

ኦሊቨር ሆታም በሰሜን ኮሪያ ዙርያ የሚሰራ ሚዲያ ተቋም ማኔጂንግ ኤዲተር ነው። ሰሜን ኮሪያ የምትለውን ለማመን እቸገራለሁ ይላል።

‹‹የማይመስል ነገር ነው፤ ከቻይናና ከደቡብ ኮሪያ የምትጎራበት አገር ናት። በተለይ ከቻይና ጋር በጥብቅ ንግድ ተሳስራለች። እንዴት ታዲያ ራሷን ጠብቃ መቆየት ይቻላታል?››

ሆኖም ኦሊቨር ኮሮና በሰሜን ኮሪያ ውስጥ ቢኖርም በወረርሽኝ ደረጃ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል ብሎ አያምንም። ቶሎ ብለው የወሰዷቸው እርምጃዎች ይህ እንዳይሆን እንዳደረገ ይገመታል።

ሰሜን ኮሪያ ወረርሽኙ በቻይና ገና እንደተከሰተ ነበር እርምጃ መውሰድ የጀመረችው፤ ድንበር መዝጋት፣ የውጭ ዜጎችን ለይቶ ማስቀመጥ፣ ወዘተ።

እንደ ኤን ኬ ዜና ጣቢያ ከሆነ ደግሞ መጀመርያ አካባቢ 10 ሺ ዜጎችን ለይታ አስቀምጣ ነበር፤ አሁንም ድረስ 500 የሚሆኑት ከዚያ አልወጡም።

ሰሜን ኮሪያዊየን ስለ ቫይረሱ ሰምተው ይሆን?

ሚስተር ሆታን እንደሚለው አብዛኛው ሰሜን ኮሪያዊ በዓለም ላይ ምን እየተከናወነ እንደሆነ መረጃ ላይኖረው ይችላል።

ሆኖም ሰሜን ኮሪያ ወረርሽኙን ለማቆም ያደረገችው ተግባር በየጊዜው በአገር ውስጥ ሚዲያ በስፋት ይነገራል። ስለዚህ መረጃው በስፋት አለ ማለት ነው።

ፍዮዶር ቴትስኪ ደግሞ በኩክሚን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ሰሜን ኮሪያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ቀልብ የሚሰውር ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አለ። በዚያውም ሕዝቡን በንጽህና አጠባበቅ ጉዳይና ቫይረሱን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ያስተምራሉ።

ሰሜን ኮሪያ በቂ የጤና መሠረተ ልማት አላት?

የዚህ ጥያቄ መልስ አዎ የሚል ነው።

ብዙዎች ሰሜን ኮሪያ በዚህ ረገድ የተንኮታኮተች አገር አድርገው ነው የሚያስቧት። ይህ ግን እውነት አይደለም።

ሚስተር ቴርቲስኪ እንደሚሉት የሰሜን ኮሪያ የጤና መሠረተ ልማት ከርሷ ጋር በጂዲፒ ተቀራራቢ ከሆኑ አገራት ጋር ሲነጻጻር እጅግ እጅግ የተሻለ ነው።

‹‹ያደረጉት ምንድነው… ብዙ የጤና ባለሞያን አሰልጥነዋል፤ ብዙ ሐኪሞች አሏቸው፤ ምንም እንኳ የሚከፈላቸው ኢምንት ቢሆንም፤ ሆኖም የጤና አቅርቦትን ለሕዝባቸው በአጥጋቢ ሁኔታ የሚሰጡ ናቸው።››

ያም ሆኖ በአገሪቱ የተጣለው ማእቀብ በቂ የጤና ግብአቶችን እንዳትሸምት አድርጓታል።

ሚስተር ሆቶም በበኩላቸው የጤና አቅርቦቱ በፕዮንግያንግ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በገጠሪቱ ሰሜን ኮሪያ ግን የሚታሰብ አይደለም ይላሉ።

በገጠር መብራትና ውሃ የሌላቸው ሆስፒታሎችን ልታገኝ ትችላለህ ይላሉ ሚስተር ሆቶም

ሰሜን ኮሪያ ኮሮና ቢኖርባት ለምን ትደብቃለች?

ለሰሜን ኮሪያ ቫይረሱ ወደ አገሪቱ መግባቱን ማመን ሽንፈት ተደርጎ ነው የሚታሰበው።

ሚስተር ሆታም እንደሚሉት አገሪቱ ቫይረሱ እንዳልገባ ብዙ ፕሮፓጋንዳ ስለነዛችና ለመከላከልም ብዙ ርቀት ስለተጓዘች ቫይረሱ ቢገባም ገባ ለማለት ከባድ ይሆንባታል።

በዚያ ላይ ሰሜን ኮሪያ የሽንፈት ተምሳሌት ተደርጋ እንድትሳል አትፈቅድም።

‹‹በዚያች አገር ስለ ሰሜን ኮሪያ መልካም የማይመስል መረጃ መስጠት አሳፋሪ ነገር ነው። በዚያች አገር ያልተጻፈ የአሰራር ባህል ‹‹መልካም ነገር ካልሆነ ዝም በል›› የሚል መርህን የሚከተል ነው። ይሉ ተመራማሪው ሚስተር ቴርቲትስኪ።