ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና የአየር መንገዶች የገቢ ማሽቆለቆል ስጋት
እኤአ በ2019 መጨረሻ ላይ በቻይና የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አየር መንገዶችን 29.3 ቢሊየን ዶላር ገደማ ያከስራቸዋል ሲል ዓለም አቀፉ የአየር መጓጓዣ ማህበር አስጠነቀቀ።
ዓለም አቀፉ የአየር መጓጓዣ ማህበር (IATA) ከአስርት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፕላን ለመጓዝ ያለው ፍላጎት ሊቀንስ ይችላል ሲል ተንብይዋል።
በዚህም በዋናነት የሚጎዱት በቻይና የሚገኙ አየር መንገዶችና በእስያ ፓሲፊክ አካባቢ የሚገኙ አገራት መሆናቸውን አስቀምጧል።
ይህ ትንበያ የተሰማው በርካታ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ለመቀነስ ብሎም ለማቋረጥ በተገደዱበት በዚህ ወቅት ነው።
እንደ ዓለም አቀፉ የአየር መጓጓዣ ማህበር ትንበያ ከሆነ፤ በአጠቃላይ እኤአ በ2020 በእስያ ፓሲፊክ የሚገኙ አገራት 27.8 ቢሊየን ዶላር ገቢ ኪሳራ እንደሚገጥማቸው ተተንብይዋል።
ከእስያ ውጪ ያሉ አገራት ደግሞ 1.5 ቢሊየን ዶላር የገቢ ማሽቆልቆል ይገጥማቸዋል ተብሏል።
የማህበሩ ዳይሬክተር የሆኑት አሌክሳንደር ዲ ጁኒያክ በመግለጫቸው ላይ እንዳስቀመጡት "አየር መንገዶች አንዳንዴ ሙሉ በሙሉ፣ አንዳንዴ ደግሞ የበረራውን ብዛት በመቀነስ ከባዱን ውሳኔ እየወሰኑ ነው። ይህ ዓመት ለአየር መንገዶች ፈታኙ ዓመት ይሆናል...።"
ማህበሩ አክሎም ይህ ቢሆንም እንኳ የዚህ የገቢ ማሽቆልቆል በአየር መንገዶቹ ትርፋማነት ላይ ያለውን ተጽዕኖ ለመናገር ጊዜው ገና መሆኑን ገልጿል።
ዓለም አቀፉ የአየር መጓጓዣ ማህበር እኤአ በ2003 የሳርስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅትም እንዲህ አይነት ትንበያ አስቀምጦ ነበር።
በወቅቱ ወረርሽኙ ለስድስት ወራት ብቻ የዘለቀ ሲሆን በአውሮፕላን ለመጓዝ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ወረርሽኙ ሲያቆም ደግሞ በፍጥነት አንሰራርቷል።
የሳርስ ወረርሽኝ ተከስቶ በነበረበት ዓመት፤ በእስያ ፓሲፊክ የሚገኙ አየር መንገዶች በ5.1 በመቶ የደንበኞች መቀነስ ገጥሟቸው ነበር።
ምንም እንኳ የበሽታው ወረርሽኝ በቻይና ብቻ ተወስኖ ይቀራል የሚል ትንበያ ቢኖርም ተጽዕኖው ግን ሰፊ እንደሚሆን ተተንብዮ ነበር።
ዓለም አቀፉ የአየር መጓጓዣ ማህበር (IATA) እስያ ፓሲፊክ ከ2015 እስከ 2035 ባለው ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ በአውሮፕላን ተጓዥ የሚኖርበት አካባቢ ነው ሲል መተንበዩ ይታወሳል። ይህም ማለት በአራትና በአምስት እጥፍ የሚያድግ የአየር መንገዶች ገበያ እንደሚኖር የተተነበየበት ነበር።
በትናንትናው ዕለት የአውስትራሊያው ቃንታስ አየር መንገድ እና የአውሮፓው ኤር ፍራንስ ኬኤልኤም በኮሮና ቫይረስ ወረርረሽኝ ምክንያት በዚህ ዓመት የገቢ ማሽቆልቆል እንደሚገጥማቸው አስታውቀው ነበር።