የታይላንድ ባለስልጣናት አደንዛዥ ዕጽ የተደበቀበትን መኪና ለጨረታ አቀረቡ

የታይላንድ ባለስልጣናት በስህተት አደንዛዥ ዕጽ የተደበቀበትን መኪና ለጨረታ አቀረቡ።

ባለስልጣናቱ መኪና ለመሸጥ ባወጡት ጨረታ መሰረት ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚከፍል ገዥ ተገኝቷል። ሲአር-ቪ የተሰኘችውን መኪና ከበርካታ ፈላጊዎች ጋር ተወዳድሮ አንድ ግለሰብ አሸንፏል። 19 ሺ የአሜሪካን ዶላር ወይም 570 ሺ ብር አካባቢ ደግሞ ጨረታውን ያሸነፈበት ዋጋ ነው።

መኪናው ባለፈው ዓመት ፖሊስ የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎችን ሲያድን ይዞ የወረሰው ነበር።

ነገር ግን ግዥው ተፈጽሞ ገዥ መኪናውን ሊያስፈትሽ ጋራጅ ሲወስደው የጋራጁ መካኒክ በመኪናው ሆድ ዕቃ ውስጥ ያልተለመደ ነገር አግኝቷል። በክኒን መልኩ የተቀመሙ 94 ሺ አደንዛዥ ዕጾች።

በአገረ ታይላንድ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚያዙ መኪናዎችን ፖሊስ በሚገባ ይፈትሻል። ይህም መኪና ፖሊስ በቂ ነው ያለው ፍተሻ ተተግብሮበታል። ነገር ግን አዘዋዋሪዎቹ በደንብ ደብቀውት ስለነበር ከዕይታ ሰውረውታል።

ከተሽከርካሪው በስተጀርባ በሚስጥር ክፍል ውስጥ ተደብቀው በሚገኙ ሳጥኖች ውስጥ ክኒኖቹ መገኘታቸውን የአካባቢው ከፍተኛ ሹም ሚስተር ሊሪስሪስ ለባንኮክ ፖስት አረጋግጠዋል። በመሆኑም አሁንም ተጨማሪ አደንዛዥ ዕጽ ሊኖር ስለሚችል የመኪናዋ ሆድ ዕቃን የመበርበሩ ጉዳይ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል ሹሙ።

ባለፈው ዓመት መኪናዋ ስትያዝ 100 ሺ ተመሳሳይ የአደንዛዥ ዕጽ ክኒኖች ተገኝተው ነበር። የተገኘው አደንዛዥ ዕፅ ወንጀሉን አቀናብረዋል ለተባሉት ግለሰቦች የወንጀል ማክበጃ የሚደረግ ሲሆን መካኒኩና የመኪናዋን በጨረታ የገዛው ግለሰብ ይህ ተጨማሪ አደንዛዥ ዕጽ እንዲገኝ ላደረጉት ትብብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

"ያባ" የሚል ስያሜ ያለው ይህ አደንዛዥ ዕጽ ትርጓሜውም "የእብድ መድኃኒት" ማለት ሲሆን በሕገ ወጥ መልኩ ከምያንማር ወደ ታይላንድ እየገባ በርካሽ በቀይ ወይም ሐምራዊ ክኒኖች ይሸጣል።

የታይላንድ መንግሥት በ2018 ብቻ 516 ሚሊዮን ተመሳሳይ የአደንዛዥ እጾችን ይዟል።