ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሜጋንና ሃሪ የቤተ-መንግሥት ኃላፊነት በቃኝ ማለታቸው የእንግሊዝ ንጉሳዊ ቤተሰብን አስቆጥቷል
የሱሴክስ ንጉስ እና ንግስት በመባል የሚታወቁት ሜጋን ሜርከልና ልዑል ሃሪ የቤተ-መንግሥት ኃላፊነት ይብቃን ማለታቸው የተሰማው ትላንት ምሽት ነው።
ሜጋንና ሃሪ ውሳኔውን የወሰኑት የእንግሊዝ ንጉሳዊ ቤተሰብን ሳያማክሩ መሆኑ ልዑላኑን እንዳስቆጣ ቢቢሲ መረዳት ችሏል።
የባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ልዑላን ምንም እንኳ ስለ ሜጋንና ሃሪ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመምከር ላይ የነበሩ ቢሆንም ይህንን ውሳኔ አልጠበቁትም ነበር ተብሏል።
ዕለተ ረቡዕ ውሳኔያቸውን አስመልክተው የፅሑፍ ሃተታ የለቀቁት ሜጋንና ሃሪ ውሳኔው ላይ የደረሱት ለበርካታ ወራት ከመከርንና ከዘከርን በኋላ ነው ብለዋል።
ባልና ሚስቱ ከነባር የቤተ-መንግሥት ኃላፊነታቸው ወርደው በገንዘብ ራሳቸውን ለመቻል እንደሚጥሩም አሳውቀዋል።
አልፎም ከዚህ በኋላ ተቀማጭነታቸውን በእንግሊዝና በሰሜን አሜሪካ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ለንግስቲቱ ተገዥነታችን ግን ሁሌም ይቀጥላል ሲሉም በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
«እንግሊዝም ሆነ አሜሪካ መመላለሳችን ለልጃችን መልካም አጋጣሚ ነው። ምክንያቱም የእንግሊዝ ንጉሳዊ ቤተሰቡን እንዳይረሳ ያግዘዋል። አልፎም ስለወደፊታችን እንድናስብ ይረዳል።»
ባልና ሚስቱ የሱሴክስ ልዑላዊ እርዳታ ድርጅት አቋቁመው በአፍሪካና አሜሪካ በመዘዋወር ሴቶችን ለማበረታታት እንደሚሠሩ ይፋ አድርገዋል።
የባልና ሚስቱ ውሳኔ ወደፊት ምን ዓይነት የቤተ-መንግሥት ኃላፊነት ነው የሚኖራቸው የሚል ጥያቄን መጫሩ አልቀረም።
ነገር ግን ለሜጋንና ቧላ ተራ ሕይወት መምራት እጅግ ከባድ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። ዋነኛው ምክንያት ደግሞ መገናኛ ብዙሃን ለጥንዶቸ የሚሰጡት ትኩረት ነው።
ተንታኞች፤ ጥንዶቹ ከመጋባታቸው በፊትም ቢሆን ሚስት በትወና፤ ባል ደግሞ በልዑልነቱ ታዋቂ የነበሩ በመሆናቸው ሕይወት ቀላል ይሆንላቸዋል ብሎ ማሰብ ዘብት ነው ባይ ናቸው።
እንደውም መገናኛ ብዙሃን ጥንዶቹን አጥምዶ የዜና ማዕድ ላይ ለማቅረብ ከመቼውም የበለጠ ይተጋሉ፤ ምክንያቱም ባልና ሚስቱ ከሌሎች ንጉሳውያን ቤተሰብ አባላት ወጣ ባለ ተግባራቸው ይታወቃሉና።
ብዙዎች ከንጉሳዊ ተግባራት በማፈንገጥ የምትታወሰው የልዑል ሃሪ እናት ልዕልት ዳያናን ከጥንዶቹ ባሕሪይ ጋር ያመሳስሉታል።
ቢሆንም ውሳኔያቸውን ንጉሳዊ ቤተሰቡን ሳያሳውቁ ይፋ ማድረጋቸው ግራ አጋቢ ነው የሚሉ አልጠፉም። ምንም ቢሆን ለንጉሳዊው ቤተሰብ ኃላፊነት አለባቸው ሲሉ አመክንዮዋቸውን ያስቀምጣሉ።
አልፎም ጥንዶቹ ከቤተ-መንግሥት ኃላፊነታቸው ከወረዱ በኋላ ለኑሯቸው እና ደህንነታቸው ክፍያውን የሚፈፅመው ማነው የሚለው የግብር ከፋዩ ጥያቄ እንደሆነ ይዘገባል። ጥንዶቹ በገንዘብ ራሳችንን እንችላለን ይበሉ እንጂ ለጊዜው የቤተ-መንግሥት ገንዘብ እንደሚጠቀሙ ይታወቃል።
ከቤተ-መንግሥት ከወጡ የት ነው የሚኖሩት? ማነውስ በገንዘብ የሚረዳቸው? ከሎሎች ንጉሳውያን ቤተሰብ አባላት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነትስ? ያልተመለሱ ጥያቄዎች ናቸው።
ሌላው እንግሊዛውያንን እያነጋገረ ያለው ጉዳይ ንጉሳዊው ቤተሰብ እያከተመ ይሆን ወይ የሚለው ነው።
ጥንዶቹ በተለይ የእንግሊዝ መገናኛ ብዙሃን አላስቀምጥ እንዳሏቸው እሙን ነው። ሜይል የተሰኘውን ጋዜጣ መክሰሳቸውም ይታወሳል።