ትራምፕ ሜጋን መርኬልን 'አስቀያሚ' ብዬ አልሰደብኩም በማለት ካዱ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሜጋን መርኬልን "አስቀያሚ" ሲሉ መሳደባቸው የተቀረፀ ቢሆንም እርሳቸው ግን ምን ሲደረግ በማለት ክደዋል።

እሁድ እለት በቲውተር ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት "ሜጋንን 'አስቀያሚ' ስል አልጠራኋትም" በማለት "ይህ የሐሰተኛ መገናኛ ብዙኃን እንቶ ፈንቶ ነው፤ ለዚህም እጅ ከፍንጅ ተይዘውበታል" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስለ መርኬል አስተያየታቸውን የሰጡት የእንግሊዝ ጉብኝታቸውን ከማድረጋቸው በፊት ከ ዘ ሰን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት ነበር።

የቀድሞ ተዋናይቷና የአሁኗ የሰሴክሷ ንግስት መርኬል የትራምፕ ሁነኛ ተቺ ነበረች።

በ2016 በተካሄደው የአሜሪካ ምርጫ ፉክክር ወቅት ተቀናቃኛቸውን ዲሞክራቷን ሒላሪን ክሊንተንን በመደገፍ ፕሬዝዳንት ትራምፕን "ከፋፋይ" እና "ሴት ጠል" በማለት ነቅፋቸዋለች።

ከጋዜጣው ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ ይህ አስተያየቷ የተነገራቸውና የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ መስማታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም "ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም፤ ምን ማለት ይቻላል? ብቻ አስቀያሚ ናት" ብለዋል።

በመቀጠልም የንጉሳዊ ቤተሰቦችን በመቀላቀሏ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው "በጣም ጥሩ" ልዕልት ይወጣታል ብለዋል።

ቅዳሜ እለት የቃለምልልሱን ድምፅ ዘ ሰን የለጠፈው ሲሆን ትራምፕ ይህንን ማለታቸው ከካዱ በኋላ በርካቶች አስተያየታችን ሰጥተዋል።