ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሶማሊያውያን፤ አውስትራሊያን ግመሎቻችን ትመልስ የሚል ጥያቄ አቅርበዋል
በደቡብ አውስትራሊያ በተከሰተው ከፍተኛ ድርቅና ሙቀት የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ግመሎች በአልሞ ተኳሽ ጥይት እየተገደሉ መሆኑ ተሰምቷል።
እነዚህ በአውስትራሊያ የዱር እንስሳት የሆኑት ግመሎች በጥይት እየተገደሉ መሆኑን የሰሙ ሶማሌያውያን ግን ዜናው አስቆጥቷቸዋል።
አውስትራሊያ አምስት ቀን ይፈጅብኛል ባለችው ግመሎችን የመግደል ዘመቻ ሂሊኮፕተርን የምትጠቀም ሲሆን ለመግደሏ ምክንያት የሆነው ደግሞ በድርቅና በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ግመሎቹ ውሃ ፍለጋ ወደ ሰው መኖሪያ መሄዳቸውና የአካባቢው ነዋሪዎች ለደህንነታቸው በመስጋት በማመልከታቸው ነው።
በዚህ የተቆጡ ሶማሌያውያን ግመሎቻችንን ላኩልን እኛው እንከባከባቸዋለን ሲሉ ተደምጠዋል።
በአውስትራሊያ ያሉት ግመሎች በቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ ባይታወቅም በመቶ ሺህዎች እንደሚቆጠሩ ይገመታል።
እነዚህ ግመሎች ከሚኖሩበት ዱር ወደ ሰው መኖሪያ አካባቢ በመምጣት አጥሮቻቸውን ማፈራረስ፣ ሰው መተናኮል እንዲሁም ውሃቸውን መጠጣት መጀመራቸው ተነግሯል።
ከትናንት ጀምሮ የግመሎቹን እንቅስቃሴ ለመግታት በሂሊኮፕተር በመታገዝ ከሰው መኖሪያ ለማስወገድ በሚል በአልሞ ተኳሾች መግደል ተጀምሯል።
ለግመል ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው ሶማሊያውያን ታዲያ ይህ ለምን ይሆናል በሚል ግመሎቹን ወደ ትውልድ መንደራችን መልሱልን ሲሉ ጠይቀዋል።
ሶማሊያውያን ግመሎቹ ከእኛ የተወሰዱት በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ሶማሌላንድን ታስተዳድር በነበረችው ብሪታኒያ ነው ይላሉ።
ሌሎች ግን ግመሎች በአውስትራሊያ የሚኖሩ ብሪታንያውያን ከሕንድ፣ አፍጋኒስታንና ከመካከለኛው ምስራቅ በመውሰድ የአውስትራሊያ በረሃ ላይ እንዲለምዱ አድርገዋቸዋል ሲሉ ይናገራሉ።
የሶማሌላንድ ግመል አርቢዎች ማህበር ሊቀመንበር ሙስጠፌ አሊ ዲቅ እንስሳቶቹ ለሱማሌያውያን "እጅግ የተከበሩ ናቸው" ከሰው ቀጥሎ ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም አውስትራሊያ የግመሎቹን ሕይወት መጀመሪያ ወደ ተወሰዱበት በመመለስ ልታተርፋቸው ይገባል ሲሉ ይጠይቃሉ።
ሌሎች ደግሞ በትዊተር ገጻቸው ላይ ይምጡ መካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ለእነሱ አይጠብም ሲሉ ተናግረዋል።
ሶማሊያውያን ምንም ያህል ገንዘብ ቢኖራቸው ሀብታቸውን የሚለኩት ባላቸው የግመል ብዛት ነው።
አውስትራሊያ በአልሞ ተኳሾች የምትገለው የዱር ግመሎቿን ብቻ ሳይሆን ፈረሶችንም ጭምር መሆኑ ታውቋል።
በአውስትራሊያ ከወራት በላይ በነበረው የእሳት ቃጠሎ 2ሺህ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን 25 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።