ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኡጋንዳውያን ለፕሬዝደንት ሙሴቪኒ ሲንበረከኩ የሚያሳየው ምስል አነጋጋሪ ሆኗል
የኡጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ለተንበረከኩላቸው አዛውንት ግራጫ ፖስታ ሲያድሉ የሚታይበት ተንቀሳቃሽ ምስል መነጋገሪያ ሆኗል።
ሙሴቪኒ ለአምስት ቀናት ጫካ ውስጥ ነው የምኖረው ብለው ዱር ከከተሙ ሶስት ቀናት ሆኗቸዋል።
በዚህ የጫካ ኑሯቸው አብሯቸው የተሳተፈ አንድ ግለሰብ ነው ሙሴቪኒ በእንብርክክ ላሉ አዛውንቶች ግራጫ ፖስታ ሲያድሉ ቪድዮ ቀርፆ ማሕበራዊ ድር-አምባዎች ላይ የለቀቀው።
ፕሬዝደንቱ ወደ ጫካ መመለስ ያስፈለጋቸው ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት በታጣቂነት ዘመናቸው ያለፉበትን ለማስታወስ ነው ተብሏል።
ሙሴቪኒ እና አጋሮቻቸው በ1978 ዓ.ም. ነው የኢዲ አሚን ዳዳን መንግሥት ገልብጠው ሥልጣን የያዙት።
ከሰሞኑ በተለቀቀው ቪዲዮ ላይ ነዋሪዎች ዝማሬ እያሰሙ፤ ሙሴቪኒ ደግሞ ወንበር ላይ ተቀምጠው በእንብርክካቸው ወደ እሳቸው ለሚጠጉ አዛውንቶች በእርዳታ መልክ ግራጫ ፖስታ ሲያድሉ ይታያሉ።
ሙሴቪኒ በግራጫ ፖስታ ውስጥ ገንዘብ እያደሉ እንደሆነ ተገምቷል
እንደ ግሪጎሪ አቆጣጠር በ2021 ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ሙሴቪኒን ይገዳደራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተቀናቃኞች መካከል የሆኑት ኪዛ ቤስጊዬ ድርጊቱ አረጋውያንን የሚያሸማቅቅ ነው ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ፅፈዋል።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ ከተለቀቀ በኋላ በርካታ ኡጋንዳውያን ድርጊቱን አውግዘውታል። አንዳንዶች ፕሬዝደንቱ ይህን የሚያደርጉት በሚቀጥለው ምርጭ ሕዝቡ እንዲመርጣቸው በማሰብ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ሙሴቪኒ ስለ ተንቀሳቃሽ ምስሉ ምንም ያሉት ነገር የለም። ይልቁንስ በጫካ ጉዟቸው አብረዋቸው የተሳተፉትን ምስጋና እንካኝ ብለዋል።
ፕሬዝደንቱ ታጣቂ በነበሩ ጊዜ ከያኔው የዩጋንዳ ፕሬዝደንት ኦቦቴ ጦር ጋር የተዋጉበትን ቦታ ጎብኝተው በሚቀጥሉት ቀናት ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ መናገሻቸው ካምፓላ ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።