ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቤሻንጉል ክልል ምክር ቤት አባል እና የኢኮኖሚ ዘርፍ ሰብሳቢ 'በታጣቂዎች' ተገደሉ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል እና የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዱላሂ ሶጃር፤ ዛሬ ማለዳ (ሐሙስ) በታጠቁ ኃይሎች በደረሰባቸው ጥቃት መገደላቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የተከበሩ አቶ አብዱላሂ ለመንግሥት ሥራ ከአሶሳ ወደ ነቀምት በመጓዝ ላይ ሳሉ መገደላቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሠ በየነ ተናግረዋል።
ጥቃቱ የተፈፀመባቸው ዛሬ ማለዳ 1፡30 ላይ ከአሶሳ ወደ ነቀምት በመጓዝ ላይ እያሉ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ቤንጓ አካባቢ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በጥቃቱም በመኪናው ውሰጥ የነበሩ አንድ ወንድና አንድሴት ላይ ጉዳት መድረሱን የተናገሩት ኃላፊ በህክምና እርዳታ ላይ እንደሚገኙም ጨምረው ገልፀዋል።
አቶ መለስ በቅርቡ አንድ የፖሊስ ኃላፊ በታጣቂዎች መገደላቸውን ገልፀው፣ ከክልሉ ተነስቶ አሮሚያ ክልልን የሚያቋርጠው መንገድ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ስጋት የነበረበት መሆኑን አስታውሰዋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመንግሥት ኃላፊዎችን ኢላማ አድርገው በታጣቂዎች ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ቢያንስ ስምንት ኃላፊዎች መገደላቸው ተነግሯል። በጥቃቱ ሌሎችም ሰዎች ሰለባ በመሆናቸው የሟቾች ቁጥር ከፍ ያለ ነው።