#9 እሷ ማናት? ከበለስ ማርማላታ በማምረት ወደ ውጪ የምትልከው ኢትዮጵያዊት

ጸጋ ገብረኪዳን እባላለሁ፤ ባለትዳርና የሁለት ሴት ልጆች እናት ነኝ። በትግራይ ሐውዜን ከተማ ተወልጄ ሰባት ዓመት ሲሞላኝ ከቤተሰቦቼ ጋር ወደ አስመራ ሄድኩኝ። እስከ 10ኛ ክፍልም እዛው አስመራ ተማርኩኝ።

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ግን፤ በ1993 ዓ.ም ከቤተሰቦቼ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ተመለስን። በዚህ ወቅት ትምህርቴንም አቋርጬ፤ ትልቅ ሰውም ሆኜ ስለነበር ሥራ እየሠራሁ ቤተሰቦችን መርዳት ግድ ይለኝ ነበር።

ከሁለት ዓመት በኋላ፤ 'እናቶች ለእናቶች' በተባለው ማኅበር ውስጥ [በ1993 ዓ.ም የተቋቋመ ማኅበር ሆኖ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ያለባቸው እናቶችን ይረዳል]፤ ጽዳትና ተላላኪ ሆኜ ተቀጠርኩኝ።

በ2005 ዓመተ ምህረት መጨረሻ አካባቢ፤ አሁን ላለሁበት ደረጃ አጋጣሚ የፈጠረልኝን ዕድል አገኘሁ። በማኅበሩ ውስጥ እየሰራሁኝ ሳለ፤ አንዲት ሜክሲኳዊት ለሴቶቹ ሥልጠና ለመስጠት መጣች።

የበለስ ተክል ከሚታወቅበት ሃገር የመጣችው ባለሙያ፤ ከዚህ ፍሬ እንዴት የተለያየ ምግብ ማዘጋጀት ይቻላል የሚል ሥልጠና ለአንድ ሳምንት ሰጠችን።

ራሴን መቀየር የዘወትር ህልሜ ስለነበር፤ ሥልጠናውን በሚገባ ወሰድኩ። ሥልጠናውን ተግባራዊ አድርጌ መሻሻል አለብኝ የሚል ውሳኔ ላይ ደርሼ ስለነበር፤ የተለያዩ ችግሮች እየገጠሙኝም ቢሆን ቀጠልኩበት።

በዚህ መሠረት ከበለስ የሚዘጋጅ ጭማቂ፣ ኩኪስና ሌሎችን ነገሮችን እያዘጋጀሁ ሰዎች እንዲያውቁት ለማድረግ ብዙ ዋጋ ከፈልኩ።

ሰው በተፈጥሮው አዲስ ነገር ቶሎ መቀበል ስለሚከብደው፤ በተለይ ማርማላታውን ማምረት ስጀምር ማመን የሚያቅታቸው፣ መቀበል የሚያስቸግራቸው በርካታ ሰዎች ይገጥሙኝ ነበር።

"የበለስ ማርማላታ ደግሞ ምንድን ነው!?" የሚሉኝ ብዙዎች ነበሩ። በወቅቱ የገንዘብ አቅምም ስላልነበረኝ በቀላሉ ከሚያጋጥሙኝ ፈተናዎች ለመውጣት እቸገር ነበር።

በለስ በቅርብ የሚገኝ ሃብታችን በመሆኑ በየቀኑ ተስፋ በማድረግ ገፋሁበት፤ እየከሰርኩም ሰው እንዲያውቀው አደረግኩኝ። በዚህ ሁሉ ተስፋ ቆርጨ አላውቅም።

አሁን?

በለስ ወርቃማ አረንጓዴ ሃብት ነው ብዬ ነው የማምነው። እስከአሁን በአግባቡ ሠርተን ጥቅም ላይ አውለነዋል ብዬ አላስብም።

በመሆኑም፤ ከበለስ የሚሠራው ማርማላታም ሆነ ጭማቂ እንዴት ቢሠራ ሰው ሊወደው ይችላል? ምን ዓይነት ጥረትና ታታሪነት ይፈልጋል? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ብዙ ጊዜ አጥፍቻለሁ።

በለስ፤ እሾሁን በአግባቡ በማስወገድ ሰላጣ፣ ጥብስ፣ ዱለት ማዘጋጀትም ይቻላል።

አልፎ አልፎ በሚዘጋጁ ዐውደ ርዕዮች ላይ እየቀረብኩኝ፤ የዚህን ምርት ጥቅምና ይዘት ለማስረዳት ረጅም ጊዜ ወሰደብኝ። ቢሆንም በጽናት ቀጠልኩ። እንዲህ ዓይነት ሥራ ብዙ ሰው ደፍሮ ስላልገባበት፤ እኔ የምችለውን ሰርቼ ራሴን በመቀየር ኀብረሰተቡን መጥቀም የምችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ።

ለብቻዬ ከምሆን ደግሞ ሌሎች አራት ሰዎች ጨምሬ "ጸጋና ንርአያ የሽርክና ማህበር" የሚል የማኑፋክቸሪግ ማኅበር በመመስረት እየሠራሁ ነው። በዚህ ማኅበር አራት ሴቶችና አንድ ወንድ አለን። ማኅበሩን በ2007 ዓ.ም ነው ያቋቋምነው።

ቀደም ብሎ፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም (ፋኦ) እና የግብርና ሚኒስቴር በመተባበር ከአንድ የጣልያን ሃገር ትልቅ ሱፐርማርኬት ጋር የገበያ ትስስር ፈጠሩልኝ፤ በዚህ አጋጣሚ 4ሺህ ጠርሙስ ማርማላታ ልኬያለሁ።

እነሱም፤ የምርቱን ብቃት በማረጋገጥ ለአንድ አመት መቆየት የሚችል ተፈጥሮአዊ ምርት መሆኑን መስክረውልኝ ገንቢ አስተያየት ሰጥተውኛል።

በቅርቡ ኳታር ከሚገኘው አንድ ትልቅ ሱፐርማርኬት ጋር ተነጋግሬያለሁ፤ እንደሚቀበሉኝም ነግረውኛል። በአገር ውስጥም እንደ ሸዋ ሱፐርማርኬት ባሉ ትልልቅ የገበያ አዳራሾች ምርቱን አስገብቼ ነበር። በዚህ አጋጣሚም ህብረተሰቡን አውቆት መጠቀም እንደሚፈልግ ተረድቻለሁ።

ግን፤ የምናመርታቸውን ምርቶች የምናሽግበት ጠርሙስ እጥረት ስለሚገጥመን፤ በምንፈልገው ልክ ገበያው ላይ ገብተን መወዳደር አልቻልንም። የማምረት አቅማችን አንሶ ሳይሆን፤ የጠርሙሱ መግዣ ዋጋ እኛ ለምርቱ ከገመትነው በላይ ስለሚሆንብን ነው።

ከአሁን በኋላስ?

በኢንተርኔት ላይ እንገኛለን። አሁን ላይ የፈጠርኩት ካፒታል ወይም ሃብት ይህ ነው ማለት ባልችልም፤ ራሴን የምችልበት ሥራ በመፍጠር ግን አዲስ ነገር ህብረተሰቡን ማስተዋወቅ ችያለሁ።

ምርቱን የምናመርተው በሰው ጉልበት ብቻ በመሆኑ፤ በቅርቡ አቅማችንን አሳድገን ዘመናዊ ግብዓት በመጠቀም ብዙ ምርት ማምረት የምንችልበት አቅም እንደምንፈጥር ተስፋ አደርጋለሁ።

ሥራችን ለማስፋት ከመንግሥት ብድር ስንጠይቅ፤ መኪናና ቤት ይጠይቁናል። ይህ ለእኛ ትልቁ ፈተናችን ነው።

ሴት ልጅ በሕይወቷ የሚፈትኗት ነገሮች ብዙ ቢሆኑም፤ ሥራን መምራት፣ ልጅ ማሳደግ፣ ቤተሰብ ማስተዳዳር አንድ ላይ ይበልጥ ይፈትኗታል። ብዙ ጊዜ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ስንቀሳቀስ፤ ልጆችን ትቼ ስለምወጣ፤ በእነሱ ሃሳቤ ወደ ኋላ ይወሰዳል፣ እሳቀቃለሁ፤ እናፍቃለሁ።

ጠንክሬ ባመንኩበት እንድቀጥል አድርጎኛል የምለው አንድ ነገር ቢኖር ያለኝ ጽናት ቢሆንም፤ ባለቤቴም በነጻነት እንድንቀሳቀስ ስለሚያግዘኝ ከስኬት ሳልደርስ ግን አልቀረሁም።

በሚቀጥሉት ዓመታት፤ የተሻሉ የበለስ ምርቶች የሚሠሩበት ኢንዱስትሪ እንዲኖረኝ እጥራለሁ።

ይህ ለብዙ ሰዎች [በተለይም ለሴቶች] የሥራ ዕድል በመፍጠር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንዲሆን፤ እንዲሁም ልጆቼ ጥንካሬን የሚማሩበት ቦታ እንዲሆን እፈልጋለሁ።

ሴቶች ጠንካራና ሥራ ፈጣሪ ነን ብዬ አምናለሁ።

ጊዜው ደግሞ ሴት ልጆችን የተሻለ ዕድል እንዲያገኙ የሚፈቅድ ስለሆነ፤ ተስፋ ሳንቆርጥ፣ ቸልተኝነት ሳናበዛ "እንዴት ግን እችለዋለሁ?" የሚል አስተሳሰብ አስወግደን ራሳችን እንድናሳድግና እንድንቀይር እማጸናለሁ።

እሷ ማናት? የሚለው ጥንቅራችን ያሰቡበትን ዓላማ ለማሳካት ብዙ ውጣውረዶችን ያሳለፉ ሴቶችን ታሪክ የምናስቃኝበት ነው።