ከአሰቃቂ የመኪና አደጋ በተአምር የተረፈችው ሴት

የ26 ዓመቷ ወጣት በሕይወት መትረፏ ተአምር ተብሏል።

ክስተቱ በደቡብ አፍሪካ፣ ፖርት ኤልዛቤት በምትባል ከተማ ዛሬ የሆነ ነው።

ተጎታች ከባድ መኪና አሽከርካሪው ልጆቹን ከፓርሰንስ ሂል ትምህርት ቤት ሊያወጣ መኪናውን እንደነገሩ አቁሞት ነበር።

ሾፌሩ ከባዱን ተሽከርካሪ የቆመበት ቦታ አቀበታማ የሚባል ነበር ይላል ፖሊስ።

ልጆቹን ከትምህርት ቤት ሊያወጣ የሄደው ሾፌር እነሱን ይዞ ሲመለስ ከባዱ መኪናው ከቆመበት ቦታ የለም።

እንዴት ከባድ ተሽከርካሪ ከዐይን ይሰወራል ብሎ መገረሙን ሳይጨርስ ሾፌሩ የሆነውን ይረዳል።

ከባድ ተሽከርካሪው ፍሬኑን በጥሶ፣ ሌላ መኪና ላይ ወጥቶ፣ ሰው ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሱን የተረዳው ኋላ ነበር።

ከባድ ተሽከርካሪው የተጫነው የቤት መኪና እጅግ በመጨፍለቁ ማንም ከዚያች የቤት መኪና ውስጥ በሕይወት ይወጣል አልተባለም ነበር።

አራት ሰዓታት በፈጀ እልህ አስጨራሽ ሂደት ግን ሕይወት ተርፏል።

ፖሊስ እንደሚለው ከባዱ ተሽከርካሪ ፍሬን በጥሶ ከአቀበት እየተንደረደረ ነው ኦፔል አዳም ሞዴል የቤት መኪና ላይ የወጣው ።

ድንገተኛ መአት የተጫናት የቤት መኪና ከአስፋልት ተመሳሰለች በሚባል ደረጃ መጨፍለቋ ነበር የብዙዎችን ተስፋ ያጨለመው።

የእርዳታ ሰጪዎች 40 ደቂቃ የፈጀ ጥረት አድርገው ልጅቱን አትርፈዋታል።

ልጅቱ ትትረፍ እንጂ ከባድ የሚባል የአካል ጉዳቶች እንዳጋጠሟት ተነግሯል።

እሷን ከዚያ ለማውጣት መኪናውን መቁረጥ አስፈላጊ ነበር።

ፖሊስ የከባድ መኪናውን ሾፌር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገበት ይገኛል።