በፍራሹ ስር 137ሺ ብር ያስቀመጠው ኬንያዊ ገንዘብ ከመቀየሩ ጋር ተያይዞ ከሰረ

ኬንያ የመገበያያ ገንዘብ መቀየሯን ተከትሎ አንድ ግለሰብ 137 ሺ ብር (4ሺ 800 ዶላር) ከጥቅም ውጭ ሆኖበታል።

ጁሊየስ ኦዲንጋ ምቦጋ የተባለው ግለሰብ 137 ሺ ብር የሚገመት ባለ አንድ ሺ የኬንያ ሺልንግ ገንዘብ ፍራሹ ስር አስቀምጦ የነበረ ሲሆን ገንዘብ ለመቀየር የተቀመጠበት ቀነ ገደብም በማለፉ ነው ለዓመታት ያጠራቀመው ገንዘብ ከጥቅም ውጪ የሆነበት።

የገንዘብ ቅየራው በሃገሪቷ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስና ለማስቀረትና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርንም ለመቆጣጠር እንዲያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

ግለሰቡ ከመንደሩ ሲያያ ግዛት ስልሳ ኪ.ሜትር ርቀት በሚገኘው የማዕከላዊ ባንክ በመገኘት አሮጌ የመገበያያ ገንዘቡን በአዲስ መልኩ ለመቀየር ሙከራ ቢያደርግም የገንዘብ መቀየሪያ ቀነ ገደቡ መጠናቀቁን ተከትሎ ለኪሳራ ተዳርጓል።

በመካኒክነት ስራ ሲተዳደር የነበረው ግለሰብ ለጡረታ ብሎ ያጠራቀመው ገንዘብ እንደሆነም ለደይሊ ኔሽን ተናግሯል።

የማዕከላዊ ባንክ አስተዳደር እንዳሳወቁት አዲስ የመገበያያ ገንዘብ የታወጀው ሰኔ አንድ ቀን ሲሆን ከመስከረም ሃያ ጀምሮ አሮጌው የመገበያያ ገንዘብ ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

አፍሪካ ታክስ ጀስቲስ ኔትወርክ የተባለ ድርጅት እንዳሳወቀው በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት ኬንያ በየአመቱ 400 ሚሊዮን ዶላር እንደምታጣ አስታውቋል።

ባንኩ እንዳስታወቀውም የገንዘብ ቅይይሩ መሳካቱንና ከዚህ በኋላ ስርአት ባለው መንገድ የገንዘብ ዝውውር እንደሚከናወን ነው።