ትራምፕ የስደተኞችን እግር በጥይት ለመምታት ሀሳብ አቅርበው ነበር ተባለ

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞች ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉዞ ለማስተጓጎል ስደተኞቹ እግራቸውን በጥይት እንዲመቱ ሀሳብ አቅርበው ነበር ተባለ።

የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኞች ያሳተሙት መጽሐፍ ላይ የተካተተው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ፕሬዘዳንቱ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ለማድረግ በኤሌክትሪክ የታጠረ የድንበር ግንብ የመገንባት ሀሳብም ሰንዝረዋል።

ትራምፕ ከምረጡኝ ቅስቀሳቸው ጀምሮ ያወሩለት የድንበር ግንብ፤ ከፔንታጎን በተመደበ 3.6 ቢሊዮን ዶላር ግንባታው መጀመሩ ይታወሳል።

ፕሬዘዳንቱ፤ ስደተኞችን ለመግታት በእባብ ወይም በአርጃኖ የተሞላ ኩሬ የማዘጋጀት ሀሳብ እንዳቀረቡም በመጽሐፉ ተካቷል። በመጽሐፉ ስለተባሉት ነገሮች እስከአሁን ከዋይት ሀውስ ምላሽ አልተሰጠም።

'ቦርደር ዋርስ' (የድንበር ጦርነቶች) የተሰኘው መጽሐፍ የተዘጋጀው ማይክል ሺር እና ጁሊ ዴቪስ በተባሉ ጋዜጠኞች ሲሆን ጋዜጠኞቹ ከተለያዩ ኃላፊዎች ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ በማጣቀስ መረጃውን በመጽሐፋቸው አካተዋል።

በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የታተመው መጽሐፉ፤ ትራምፕ የስደተኞችን እግር በጥይት ለመምታት ሀሳብ ቢያቀርቡም፤ "ሕገ ወጥ ነው" የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

ከዚህ ቀደም ፕሬዘዳንቱ የአሜሪካ ወታደሮች ድንጋይ የሚወረውሩ ስደተኞች ላይ ጥይት መተኮስ አለባቸው ማለታቸውም ይታወሳል።

ፕሬዘዳንቱ የድንበር ግርግዳው የሰውን አካል በሚበሳ ኤሌክትሪክ እንዲሠራ ሀሳብ ማቅረባቸውን መጽሐፉ ይገልጻል። ግድግዳውን በእባብ ወይም በአርጃኖ በተሞላ ኩሬ የመክበብ ሀሳብ ካቀረቡ በኋላ፤ ግንባታው ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስወጣቸውም ጠይቀው ነበር ተብሏል።

ትራምፕ የአሜሪካና የሜክሲኮን ድንበር ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት ያቀረቡት ሀሳብ አማካሪዎቻቸውን አስደንግጦ እንደነበርም በመጽሐፉ ተካቷል።